በፓርቲ እጩዎች መሰብሰብ የነበረበት የድጋፍ ፊርማ ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ተፈጻሚ እንዳይሆን ም/ቤቱ አፀደቀ
በግል ተወዳዳሪ እጩዎች መሰብሰብ የነበረበት የድጋፍ ፊርማ በ50 በመቶ ቀንሷል
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባ አምስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አፅድቋል
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባ አምስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ያጸደቀ ሲሆን፤ አንድ ረቂቅ አዋጅን ደግሞ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
ቀደም ሲል በግል ተወዳዳሪ እጩዎች መሰብሰብ የነበረበት ከአምስት ሺህ የማያንስ የድጋፍ ፊርማ በ50 በመቶ ቀንሶ ከ 2 ሺህ 500 የማያንስ እንዲሆን ፣ ለአካል ጉዳተኛ እጩዎች ደግሞ ከ3 ሺህ የማያንስ የሚለው ከ 1ሺህ 500 የማያንስ እንዲሆነ ተቀምጧል፡፡
በሌላ በኩል በፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች በሕጉ መሰረት መሰብሰብ የነበረበት የድጋፍ ፊርማ ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ብቻ ተፈጻሚ እንዳይሆን እንዲታገድ መደረጉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የሚያግዝ እንደሆነ በውሳኔ ሃሳቡ የተካተተ ሲሆን ፣ ም/ቤቱም የማሻሻያ አዋጁ ቁጥር 1135/2013 ሆኖ እንዲጸድቅ በሙሉ ድምጽ ተስማምቷል፡፡
የፌደራል የስነ-ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የወጣ ረቂቅ አዋጅ፡ የማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1136/2013 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡
በቀጣይነት የቀረበው አዋጅ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የግልግል ዳኝነት እና የእርቅ አሰራር ስርዓትን ለመደንገግ የወጣው ማሻሻያ አዋጅ፡ አዋጅ ቁጥር 1137/2013 ሆኖ በም/ቤቱ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን ለመደንገግ በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ፡ አዋጅ ቁጥር 1138/2013 ሆኖ በም/ቤቱ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ከውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ መንግስታት መካከል የዲፒሎማቲክ ፓስፖርት ለያዙ ሰዎች ቪዛን የማስቀረት ስምምነት ዲፕሎማቶችን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና በስራቸው የሚገኙ ሰራተኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፤ በቪዛ ምክንያት ይባክን የነበረውን ጊዜ እና ጉልበት በመቆጠብ ዜጎችን ወደ ሀገራቱ የሚያደርጉትን ምልልስ በማፋጠን ስራዎችን ያግዛል ተብሏል፡፡
አዋጁም አዋጅ ቁጥር 1139/2013 ሆኖ በም/ቤቱ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ የውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 923/2008 የማሻሻያ ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ በውጭ ሀገር ለስራ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ለኤጀንሲዎች የሚከፍሉት ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ለችግር እየተዳረጉ ስለመሆኑ ከም/ቤቱ አባላት አስተያየት ታክሎበታል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡም ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱን የም/ቤቱ መረጃ ያሳያል፡፡