ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ አደረገ
ፓርቲዎቹ እስከ ጥር 24 ቀን 2013 ድረስ ምልክቶቻቸውን ለቦርዱ እንዲያስገቡ መታዘዛቸው ይታወሳል
ቦርዱ በህጋዊነት ተመዝግበዋል ያላቸውን የ49 ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክት ነው ይፋ ያደረገው
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በህጋዊነት ተመዝግበዋል ያላቸውን ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋ አደረገ፡፡
ቦርዱ ይፋ ያደረገው መርምሮ ያጸደቃቸው የ49 ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክቶች ነው፡፡
6ተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማከናወን እንደሚያስችል በማሰብ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ካስቀመጣቸው ተግባራት መካከል አንደኛው ፓርቲዎች የምርጫ ምልክቶቻቸውን የሚመርጡበት/ የሚያስገቡበት መርሃ ግብር ነው።
በመርሃ ግብሩ መሰረትም ከጥር 13 ቀን እስከ ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ፓርቲዎች ምልክቶቻቸውን አስገብቷል፡፡ ቦርዱም ምልክቶቹን አጣርቶ ካጸደቀ በኋላ ፓርቲዎቹ በምርጫው ወቅት በይፋ የሚወከሉባቸውን ምልክቶች ዛሬ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ አድርጓል።
ይፋ የተደረገው ከአሁን ቀደም በቦርዱ እንደተገለጸው ሁሉ የ52 ፓርቲዎች የምርጫ ምልክት ሳይሆን በህጋዊነት ተመዝግበዋል የተባለላቸው የ49 ፓርቲዎች ምልክት ነው፡፡
ይፋ በሆኑት ምልክቶች መሰረትም ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ብርሃን በሚፈነጥቅ አምፖል ተወክሏል፡፡
ቀደም ሲል ያስገባውን ምልክት ቀይሮ እንዲያስገባ በቦርዱ ታዞ የነበረው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በሚዛን፣የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ከሰሞኑ ሲያነጋግር እንደነበረው ሁሉ በእጅ ሰዓት፣ ባልደራሱ ቀደም ሲል በነበረው በተጨበጠ እጅ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በአባገዳዎች ዘንግ ተወክለዋል፡፡
ቦርዱ ቀደም ሲል ይሆናሉ ያላቸውን 192 የምርጫ ምልክቶች አቅርቦ ነበር፡፡ ከ192ቱ ምልክቶች መካከል 92ቱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ፣50ው በግል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚወዳደሩ የግል እጩዎች ፣ 50ው ለክልል ምክር ቤት ለሚወዳደሩ የግል እጩዎች የቀረቡ ናቸው፡፡
ምልክቶቹ አይወክሉኝም የራሴን ወካይ ምልክት ለማቅረብ እና ለመጠቀም እፈልጋለሁ የሚል ፓርቲ የራሱን አቅርቦ በቦርዶ እንዲያጸድቅም ተፈቅዶለታል፡፡
መጪው ሃገራዊ ምርጫ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ/ም ይካሄዳል መባሉ የሚታወስ ነው፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዞኖች በክልል የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ በዚሁ ቀን ይካሄዳል መባሉ የሚታወስም ሲሆን የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ምርጫዎች ሰኔ 5 ቀን 2013 ዓ/ም እንደሚካሄዱ መገለጹ አይዘነጋም፡፡