የሀገር ሉአላዊነትን የሚዳፈር የውጭ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠየቀች
ለኢትዮጵያና ለዓለም ሰላም ከጥቅምት 21-27 2015 ዓ.ም ድረስ የሱባዔ የጸሎት ሳምንት አውጃለች
በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን ስምምነት ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ የምትደግፈው መሆኑን አስታውቃለች
ሀገራዊ ሉአላዊነትን በሚዳፈር መልኩ እየታየ ያለው የውጭ መንግስታት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠየቀች።
ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የ2015 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ የጥቅምት ወር ምልዓተ ጉባኤ ማጠቃለያ አስመልክቶ መግለጫ በዛሬው ዕለት ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በአገራዊ ሰላምና አንድነት ላይ መነጋገሩን ያነሱ ሲሆን፤ “ሰላም ለሀገራችን ሕዝቦች አንድነትና ለቀጣይ በልማታዊ እድገት የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማየት መሠረት መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ ሀገራዊ እርቀ ሰላም እንዲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቅርቧል” ብለዋል።
መንግስት በተለያዩ ጊዝያት የውጭ መንግስታት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እንደሚገቡ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡም ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት በፌደራል መንግስት እና በህሓት መካከል እየተካሄደ ያለው ንግግር ጣልቃገብነት እንዳጋጠመው መግለጻው ይታወሳል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ሀገራዊ ሉአላዊነትን በሚዳፈር መልኩ እየታየ ያለውን የውጭ መንግሥታት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም አሳስቧል” ሲሉም በመግለጫው አስታውቀዋል።
በሰሜኑ ኢትዮጵያም ሆነ በውጭው ዓለም አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ያለው አካሄድ ለቤተ ክርስቲያንንም ሆነ ለአገራዊ አንድነታችን መጠበቅ ሲባል እንደገና በሰከነ መንፈስ ታይቶ ወደነባሩ ማዕከላዊ አስተዳደርና አሠራር እንዲመለሱ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ጦርነት እንዲያበቃ አገራዊ ሰላምና አንድነት እንዲጠበቅ ትኩረት ባደረገ መልኩ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን ስምምነት ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ የምትደግፈው መሆኑንም አስታውቀዋል።
በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሰላሙ ፍጻሜ እንዲያገኝ የበኩሏን አስተዋጽኦ የምታበረክት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ሁሉም አካል ለሰላሙ መገኘት በትኩረት እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ በኦጽንኦት ያስገነዝባል ብለዋል።
“የሰላም ስምምነቱ በቅዱስ ሲኖዶሱ ሁልጊዜም በጉጉት ሲጠበቅ፣ ጸሎት ሲጸለይበትና የሰላም ጥረት ሲደረግበት የቆየ በመሆኑ አሁንም በየአቅጣጫው አገራዊ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል” ብለዋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የህዳሴ ድግብ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እስከሚደርስ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሁሉም ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከጥቅምት 21-27 2015 ዓ.ም ድረስ ለሰባት ዕለታት ለምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ማስፈጸሚያ የአንድ ሱባዔ የጸሎት ሳምንት መዘጋጀቱን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ያስታወቁ ሲሆን፤ በጸሎት ሳምንቱ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአለም ፍጹም ሰላም፣ ለህዝብ አንድነትና ሰላማዊ ኑሮ መገኘት፣ በጦርነት ምክንያት ከቄያቸው ለተፈናቀሉና በልዩ ልዩ ወረርሽኝ በሽታ ለተያዙ ምሕረትና ጤና እንዲያገኙ ጸሎት ይደረጋል ብለዋል።