የምስሉ መላክ ዩኤኢ በህዋ ምርምር ከሚያደርጉ ታላላቅ ሀገሮች ጋር መሰለፏን ያረጋገጠ መሆኑን ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ገልጸዋል
በአረቡ ዓለም የመጀመሪያ የሆነችውና “ፕሮብ ሆፕ” የተሰኘ ሥያሜ የተሰጣት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንኮራኩር የመጀመሪያ ምስል መላኳ ተገለጸ፡፡
መንኮራኩሯ የላከችው ምስል 25,000ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው የማርስ ፕላኔት በቅርበት የምትታይበት ነው፡፡
የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ እና የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ እና የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ ቢን ራሽድ አል ማክቱም ከሰሞኑ ወደ ማርስ የተላከችው መንኮራኩር የመጀመሪያ ምስል መላኳን አስመልክቶ በትዊተር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
መሪዎቹ መንኮራኩሯ በ 25,000 ኪ.ሜ ከፍታ ላይ ከምትገኘው ማርስ የመጀመሪያ ምስል መላኳን ገልጸዋል፡፡ የአቡዳቢ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በትዊተር ገፃቸው “ከማርስ የመጀመሪያው ምስል የመላኩ የብስራት ዜና ፣ በታሪካችን ልዩ ስፍራ ያለውና እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በህዋ ላይ ምርምር ከሚያደረጉ የዓለም ታላላቅ ሀገሮች ጋር መሰለፏን ረጋገጠ ነው” ብለዋል፡፡
ይህ ተልዕኮ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥና በቀዩ ፕላኔት ላይ ለሚደረገው ምርምር አዳዲስ አድማሶችን የሚከፍትና ለሳይንስ እና ለመጪው ጊዜ የራሱ በጎ አበረክቶ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡
በአረቡ ዓለም የመጀመሪያ የሆነችው መንኮራኩር ከቀናት በፊት ወደ ማርስ መምጠቋ በመላው የአረብ ሀገራት ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ደስታ የፈጠረ ነው፡፡ መንኮራኩሯ ማርስ ስትደርስ የሀገሪቱ መሪዎች በዱባይ በሚገኘው የጠፈር ምርምር ማዕከል ሆነው በቀጥታ ሲከታተሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዩኤኢ ወደ ማርስ ምህዋር መንኮራኩር በመላክ በዓለም አምስተኛዋ ሀገር ነች፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ወደ ምህዋሩ የገባችው መንኮራኩሯ ለሁለት ዓመታት ሳይንሳዊ ዳታዎችን እየሰበሰበች የምትልክ ይሆናል፡፡