ቻይናን በተመለከተ የሚሰራቸው ዘገባዎች አድሎአዊ እና ሀሰተኛ ናቸው በሚል ነው ቢቢሲ የታገደው
ቻይናን በተመለከተ የሚሰራቸው ዘገባዎች አድሎአዊ እና ሀሰተኛ ናቸው በሚል ነው ቢቢሲ የታገደው፡፡ የቻይናው ሲጂቲኤንም በብሪታኒያ እንዳይሰራጭ ከሳምንት በፊት ታግዷል፡፡
የቻይናው የብሮድካስቲንግ ተቆጣጣሪ ‘ቢቢሲ ወርልድ ኒውስ’ን በሀገሪቱ ከባድ የይዘት ጥሰት ፈጽሟል በሚል ከአየር ላይ ማውረዱን ይፋ አድርጓል፡፡
የቻይናውን ብሔራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አስተዳደር ጠቅሶ ሲጂቲኤን እንደዘገበው ‘ቢቢሲ ወርልድ ኒውስ’ ቻይናን የተመለከቱ ዘገባዎቹ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን አስተዳደር እንዲሁም የውጭ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ አስተዳደር ደንቦችን በከፍተኛ ሁኔታ የጣሰ ሆኖ ተገኝቷል ነው የተባለው፡፡
ቻይናን በተመለከተ ቢቢሲ የሚሰራቸው ዘገባዎች የዜና ዘገባ እውነተኛ እና ከአድሎ የነጻ መሆን አለበት ከሚሉት መስፈርቶች ጋር የሚቃረን መሆኑ የተገለጸ ሲሆን እና የቻይናን ብሄራዊ ጥቅሞች እና የህዝቡን አብሮነት የሚጻረር እንደሆነም የሀገሪቱ ብሮድካስቲንግ ተቆጣጣሪ አስታውቋል፡፡
“ቻናሉ በቻይና እንደ ባህር ማዶ ቻናል ለማሰራጨት የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች ማሟላት ባለመቻሉ ፣ ቢቢሲ ወርልድ ኒውስ በቻይና ግዛት ውስጥ አገልግሎቱን እንዲቀጥል አይፈቀደለትም፡፡ ብሔራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አስተዳደር ለአዲሱ ዓመት የቢቢሲን የስርጭት ጥያቄ አይቀበልም” ብሏል ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ በመግለጫው፡፡
የሆንግ ኮንግ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከአርብ ጀምሮ የ’ቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ’ን እና የቢቢሲ ሳምንታዊ ዜናን (ቢቢሲ ኒውስ ዊክሌ) እንደማያሰራጭ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የቢቢሲ ቃል አቀባይ ለሲኤንኤን “የቻይና ባለሥልጣናት ይህንን እርምጃ ለመውሰድ በመወሰናቸው ቅር ብሎናል፡፡ ቢቢሲ በዓለም ላይ እምነት የሚጣልበት ዓለም አቀፍ የዜና አውታር ሲሆን የዓለም ዘገባዎችን በፍትሃዊነት ፣ በገለልተኝነት የሚያቀርብ ነው” ብለዋል፡፡
የቻይናው ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ኔትዎርክ (ሲጂቲኤን)ም እንዲሁ በብሪታኒያ እንዳይሰራጭ ከሳምንት በፊት ታግዷል፡፡
ቻይና እና ብሪታንያ ከሆንግ ኮንግ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አለመግባባት መፍጠራቸው ይታወቃል፡፡ ብሪታንያ በቅኝ ግዛት ስታስተዳድራት ለነበረችው የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ያዘጋጀችው አዲስ ፓስፖርት በቻይና ተቀባይነት አለማግኘቱ ይታወሳል፡፡