የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የመጀመርያ ዙር ጥገና ጥናት ተጠናቀቀ
ከአብያተ ክርስቲያናቱ ውጭ ሆኖ ኃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶችን ለመከታተል የሚያስችሉ ዘመናዊ ስክሪኖች እንደሚገጠሙም ነው አስተዳደሩ ያስታወቀው
ጥገናው በቅርቡ እንደሚጀመርም የላሊበላ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል
የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የመጀመርያ ዙር ጥገና ጥናት ተጠናቀቆ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት መደረጉን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ጥገናው በሁለት የተለያዩ ዙሮች የሚከናወን መሆኑንም አስታውቋል፡፡
አስተዳደሩ የአብያተ ክርስቲያናቱን የጥገና ስራ በተመለከተ ከከተማው ማህበረሰብ አባላት ጋር ትናንት ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ የጥገናው የመጀመሪያው ዙር ጥናት መጠናቀቁን የገለጹት የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ ጥገናውን የሚያከናውኑ የፈረንሣይ የባለሙያዎች እና የፋይናንስ ቡድን አባላት መገኘታቸውን በመጠቆም ሥራው በቅርብ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡
የመጀመሪያው ዙር የጥገና ስራ በሁለም ህንጻ አብያተ ክርስትያናት ያጋጠሙ የመሠንጠቅ ችግሮች የሚጠገኑበት፣ ለምዕመናን ችግር የሆኑ በርካታ ጉድጓዶች የሚስተካከሉበት፣ ደረጃውን የጠበቀ የመብራት ዝርጋታ የሚሰራበት እና የድምፅ መንቀጥቀጥ የማይፈጥሩ ዘመናዊ ድምጽ ማጉያ ማይክራፎኖች የሚገጠሙበትም ነው፡፡
ከአብያተ ክርስቲያናቱ ውጭ ሆኖ ኃይማኖታዊ ስነ ስርዓቶችን ለመከታተል የሚያስችሉ ዘመናዊ ስክሪኖች የሚገጠሙበት ነውም ተብሏል፡፡
ይህን አጠቃላይ የውስጥና የውጭ የጥገና ሥራ ለመጀመር የሚያስችለው ዝግጅት ተጠናቋል ሲሉም ነው ከንቲባው ያስታወቁት፡፡
ሁለተኛው ዙር የጥገና መርሐ ግብር አብያተ ክርስቲያናቱን ለበለጠ አደጋ ዳርጓል የሚባልለት የብረት መጠለያ ተነስቶ በሌላ፤ ከቀርቀሃ በሚሰራ፣ በእሳት በማይቃጠል እና ቀላል በሆነ መጠለያ የመተካት ስራ የሚሰራበት ነው፡፡
አዲሱ መጠለያ ያለ ችግር ለቀጣዮቹ 50 ዓመታት እንዲያገለግል ሆኖ የሚዘጋጅ ነው የተባለ ሲሆን በቀላሉ ስልጠናውን ባገኙ የሃገር ውስጥ ባለሙያዎች እንዲጠገን ሆኖ የሚሰራ ነው፡፡
ይህን ለማድረግ የሚያስችለው ጥናት ተጠናቆ በሚመለከታቸው አካላት ተገምግሞ በዩኒሥኮ ለማፀደቅ በዝግጅት ላይ መኮኑንም አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
ቤተ ጊዮርጊስ ራሰን ችሎ መጠለያ ይሰራለታል ያለም ሲሆን መጠለያው ዘመናዊ ሲፈለግ የሚታጠፍና የሚዘረጋ በሪሞት ኮንትሮል ቁጥጥር ሊደረግበት የሚችል ሆኖ እንደሚሰራም ነው ያስታወቀው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በመሆን ከፍተኛ የመፍረስ አደጋ ውስጥ ይገኛሉ የተባለላቸውን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የጎበኙት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዔል ማክሮን አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጠገን ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው፡፡