ቀኑ የተከበረው “የሙዚየም መጻዒ ጊዜ፣ተሃድሶ እና አዲስ ዕይታ” በሚል መሪ ቃል ነው
በየዓመቱ ግንቦት 10 የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን ዛሬ ተከብሮ ውሏል፡፡
ቀኑ የሚከበረው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት እ.ኤ.አ በ1946 በተመሰረተው ዓለም አቀፍ የሙዚየሞች ካውንስል አስተባባሪነት ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1977 ጀምሮም በተለያዩ መሪ ቃሎች ተከብሯል፡፡
ዛሬም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች “የሙዚየም መጻዒ ጊዜ፣ተሃድሶ እና አዲስ ዕይታ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡
የኢትዮጵያው አከባበር በቅርቡ በተመሰረተው የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር እና በአዲስ አበባ ሙዚዬም ትብብር የተዘጋጀ ነው፡፡
ቀኑ በአዲስ አበባ ሙዚየም ቅጥረ ግቢ ሲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
የቀኑ መከበር “ሙዚየምች እና በሙዚየሞቻችን ያሉ ተንቀሳቃሽ ቅርሶቻችን ምን ያል ዋጋ እንዳላቸው እንድናውቅ ለማድረግ የሚያስችል ነው”ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት በአዲስ አበባ ባህል፣ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያ መ/ር መክብብ ገ/ማርያም “ቅርሶቻችንን እንዴት ልንጠብቃቸውና አልምተን ልንጠቀምባቸው እንደምንችል ግንዛቤን የምንፈጥርበትም ነው” ብለዋል፡፡
ሙዚየምን በተመለከተ የእምቅ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት በሆነው ማህበረሰብ ዘንድ ያለውን አመለካከት ለማሳደግና ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሚያስችልም ገልጸዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ገለጻ በአዲስ አበባ ብቻ ከ25 በላይ ሙዚየሞች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል 10ሩ በአብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ናቸው፡፡ ቢላሉል ሐበሺ የተሰኘ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ሙዚየምም አለ፡፡
ሙዚየሞች የኋላ ማንነታችንን የያዙ ቅርሶቻችን የሚቀመጡባቸው ናቸው የሚሉት ባለሙያው ለእይታ በሚመች መልኩ ሊደራጁ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ከአከባበር ስነ ስርዓቱ አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆነው የቱሪዝም ጋዜጠኛው ዑመር መሃመድ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ሙዚየሞች “አብዛኞቹ አደጋ ላይ ናቸው” ሲል ይናገራል፡፡
“ያላካልለነው ሙዚየም የለም” ሲል ብዙዎቹን መጎብኘቱን የሚገልጸው ጋዜጠኛ ዑመር የአባ ጅፋርን ቤተመንግስት በማሳያነት በማንሳት ነው ብዙዎቹ አደጋ ላይ ናቸው የሚለው፡፡
የቀኑ መከበር “ሙዚየሞቹ ትኩረት እንዲያገኙ፣ ያልታዩት እንዲታዩ፣ እንደ አዲስ መመዝገብ ያለባቸው ቅርሶችም እንዲመዘገቡና አዳዲስ ሙዚየሞች እንዲቋቋሙ ለማድረግ ያስችላል፤ ለዚህ እንሰራለን”ም ይላል፡፡
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ 13 ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡