ኢትዮጵያ የብዝሓ-ሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያን አስመረቀች
ኢትዮጵያ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም የመጀመሪያዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ማምጠቋ ይታወሳል
መቀበያው ከ5 የተለያዩ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች መረጃን ለመቀበል የሚያስችል ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ማዕከል ያስገነባዉን 7.3 ሜትር የብዝሓ-ሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ እያስመረቀ ነው፡፡
የመረጃ መቀበያ ጣቢያው ሳተላይቶችን በመቆጣጠር እና መረጃ በመቀበል በአግባቡ ተልዕኳቸውን እንዲፈጽሙ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
ከ5 የተለያዩ አለም አቀፍ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች እስከ 0.5 ሜትር የምስል ጥራት የሳተላይት መረጃን ለመቀበል እንደሚያስችልም ነው የተገለጸው፡፡
ኢትዮጵያ በታህሳስ ወር 2012 ዓ.ም የመጀመሪያዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት (ETRSS-1) ማምጠቋ ይታወሳል፡፡
ET-SMART-RSS የተሰኘች ሳተላይት ማምጠቋም አይዘነጋም፡፡
ሳተላይቷ ኢንስቲትዩቱ ከመጠቀችበት ዕለት አንስቶ የቁጥጥርና መረጃ የመቀበል ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሳተላይቷ ከቻይና መንግስት ጋር በተደረገ የትብብር ስምምነት አማካኝነት የበለፀገችና የመጠቀች ሲሆን ከሳተላይቷ የሚገኝ መረጃም ለልዩ ልዩ ሃገራዊ የልማት አገልግሎት ስራዎች እየዋለ ይገኛል እንደ ኢንስቲትዩቱ ገለጻ፡፡
ከሳተላይቷ የሚገኘው መረጃ እንደ ሃገር እያደገ የመጣውን የመረጃ ፍላጎት በዓይነት፣ በጥራት እና በመጠን ከማሟላት አንፃር ዉሱንነት አለበት፡፡
ውስንነቱን ለመቅረፍ አንድም ከፍተኛ መጠን ያለው ሳተላይት መገንባት አልያም የሳተላይት መረጃዎችን ከውጭ አቅራቢዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በግዥ ማግኘት ነው፡፡
ግንባታዉ የተጠናቀቀዉ የመረጃ መቀበያም ግልጋሎትም ይህንኑ ውስንነት መቅረፍ ነው፡፡
መቀበያው ከአምስት የተለያዩ አለም አቀፍ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች እስከ 0.5 ሜትር የምስል ጥራት ያለው የሳተላይት መረጃ ለመቀበል እንደሚያስችል ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
3 ዓመታትን ፈጅቷል የተባለለት የመቀበያ ጣቢያው ግንባታ 3 ሚሊየን ዩሮ ስለመውሰዱ ተነግሮለታል፡፡