መኪና በቤኪንግ ፓውደር፤ አውሮፓንን በማዳበሪያ በመጠቀም ማንቀሳቀስ የሚቻልበት ጊዜ ተቃርቧል- ተመራማሪዎች
የኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዎች አዲስ የባትሪ ግኝት ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል
አዲሱ ፈጠራ የምድር እና አየር ላይ ትራንስፖርት ባትሪዎችን አዲስ ለውጥ ያመጣል ተብሏል
የዓለማችንን ትራንስፖርት ሊቀይር የሚችል ፈጠራ መገኘቱ ተገለጸ።
የእንግሊዙ ኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ ተመራራማሪዎች እንዳሉት ከፈረንጆቹ 1980ዎቹ ጀምሮ ዓለም ሊቲየም ሰራሽ ባትሪዎችን ሲጠቀም ቆይቷል።
በዩንቨርሲቲው የኬሚስት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ቢል ዴቪድ እንዳሉት የሊቲየም ሰራሽ ባትሪዎችን የሚተካ አዲስ ፈጠራ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
እንደ ዴይሊ ሜይል ዘገባ ከሆነ ተመራማሪው ለተሸከርካሪዎች የሚያገለግል ባትሪ ከሶዲየም ጨው ማምረት እንደሚቻል አረጋግጠዋል።
ተመራማሪው በተለይም የሶዲየም ጨው ሀብት በብዙ ሀገራት በቀላሉ መገኘቱ እና በቤተ ሙከራ ማምረት መቻሉ ሰዎች ምርቱን በርካሽ ዋጋ እንዲገዙ ከማስቻሉም በላይ ለአካባቢ ጥበቃ የራሱን በጎ አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል።
እንዲሁም ለአውሮፕላኖች ደግሞ ከአሞኒያ ማዳበሪያ መሰራት የሚችል ባትሪ መጠቀም እንደሚችሉ ይሄው ምርምር ላይ ተጠቅሷል።
ይህ አዲስ ፈጠራ በመጪዎቹ 10 ዓመታት ውስጥ የዓለመችንን ትራንስፖርት እንዱስትሪ ሙሉ ለሙሉ ሊጠቀሙት እንደሚችሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።
ዓለማችን አሁን ላይ አብዛኞቹ ባትሪዎች ሊቲየም ሰራሽ ባትሪን በመጠቀም ላይ ሲሆኑ በተለይም የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች፣ የእጅ ስልኮች እና ሌሎች ምርቶች ዋነኞቹ ተጠቃሚዎች ናቸው።
አሁን ላይ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሸከርካሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊቲየም ሰራሽ ባተሪዎችን እየተጠቀሙ ሲሆን በቀርብ ዓመታት ውስጥ ደግሞ ወደ ሶዲየም ሰራሽ ባትሪ ፊታቸውን እንደሚያዞሩ ተገልጿል።