በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ሞቱ
“ጉርብትና ያስተሳሰረን የማንለያይ ህዝቦች ነን” ያሉት ኑረዳዒ ግድቡ ለሱዳናውያን ጭምር የላቀ አበርክቶ እንዳለው በመጠቆም የኢትዮጵያን ሰላም የሚያውክ ማንኛውም ችግር እንዳይፈጠር እሰራለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው
አብዱረሃማን ኑረዳኢም የሞቱት ዛሬ ማለዳ ወደ ካርቱም በመጓዝ ላይ ሳሉ በገጠማቸው የመኪና አደጋ ነው
በቅርቡ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማጠናከር በሚል ወደ ኢትዮጵያ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መጥተው የነበሩት በሱዳን የብሉ ናይል ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ሞቱ፡፡
አብዱረሃማን ኑረዳኢም የሞቱት ዛሬ ማለዳ ወደ ካርቱም በመጓዝ ላይ ሳሉ በገጠማቸው የመኪና አደጋ ነው፡፡
ኑረዳኢም ካርቱም መደኒ በተባለ የፍጥነት መንገድ ላይ ይጓዙ እንደነበር የሃገሪቱ ዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያዊያን አልፎ ለጎረቤት ሱዳናዊያን ጭምር የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን በአሶሳ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው በሁሉም ዘርፎች የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ድጋፍ ለማበርከት ቃል ገብተው የነበረ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ኑረዳኢም የተለያዩ የጦር መኮንኖች፣ ኮምሽነሮች እና ከፍተኛ የካቢኔ አባላቶቻቸውን ይዘው ነበር ወደ አሶሳ የመጡት፡፡
በውይይቱም በሁለቱ ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ መክረዋል፡፡
በምክክሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የክልል መንግስታቱ በየአመቱ እየተገናኙ በሰላም እና የጸጥታ ስራዎች በተለይም በድንበር ተሻጋሪ ወንጀል እና ህገወጥ የጠረፍ ንግድ እንዲሁም የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ውጤታማ ስራዎችን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ተናግረው ነበረ፡፡
የብሉናይል ግዛት አስተዳዳሪው ኑረዳኢም በግድቡ የጋራ ጠቃሚነት ላይ ያላቸውን አቋም በየጊዜው የሚገልጹ መሆናቸውን አስታውሰው እገዛቸውን እስከ ፕሮጀክቱ ፍጻሜ ድረስ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለው ነበረ፡፡
በሱዳን ሰላማዊ ሽግግር ኢትዮጵያ ለነበራት በጎ አስተዋጽኦ ያመሰገኑት ኑረዳኢም በበኩላቸው “ጉርብትና ያስተሳሰረን የማንለያይ ህዝቦች ነን” በማለት የኢትዮጵያን ሰላም የሚያውክ ማንኛውም ጉዳይ በሱዳን በኩል እንደማይኖር እና እንዳይፈጠርም በጋራ ጠንክረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን በመድረኩ ገልጸው ነበረ፡፡
በየ 6 ወራቱ የሚካሄደው የሁለትዮሹ ውይይት በቀጣይ ኑረዳኢም በሌሉበት በብሉ ናይል ግዛት የሚካሄድ ይሆናል፡፡