ዛሬ በሱዳን የተለያዩ ከተሞች ሁለት አይነት ሰልፎች ተካሒደዋል
በዳቦ ዋጋ መናር ምክንያት ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ከስልጣን እንዲነሱ ያደረገው የሱዳን አብዮት ሁለተኛ ዓመቱ በተለያዩ ስሜቶች እየታሰበ ነው፡፡
ከዛሬ ሁለት ዓመት ወዲህ ፕሬዝዳንት አልበሽርን በመጣል አዲስ የሽግግር መንግስት የተቋቋመ ሲሆን ወታደሩንና ሲቪሉን የሚወክሉ መሪዎች ሀገሪቱን እያስተዳደሩ ነው፡፡ ዛሬ ካርቱምን ጨምሮ በሱዳን የተለያዩ ከተሞች በተካሔዱ ሰልፎች በአንድ ወገን አብዮቱን የሚደግፉ አካላት በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎችም ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
አብዮቱን በመደገፍ ሰልፍ የወጡ ሰልፈኞች የአብዮቱ ዓላማ ግን መስመሩን መሳቱን በመጥቀስ ቁጣቸውን አሰምተዋል፡፡ የኑሮ ውድነት እና የኢኮኖሚ ቀውስን በመቃወም ከሁለት ዓመት በፊት አብዮት ቢፈነዳም እነዚህን ችግሮች ከመቅረፍ አንጻር አብዮቱ ምንም አልፈየደም በሚል የተቃውሞ ድምጾች ተስተጋብተዋል፡፡ በሱዳን ያለው የኑሮ ውድነት ፣ ከፍተኛ የዳቦ እጥረት እና የሀገሪሩ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
ከአብዮቱ በተቃራኒ በመቆም የፕሬዝዳንት አልበሽርን መንግሥት በመደገፍ አደባባይ የወጡም አሉ፡፡ እነዚህ አካላት የአልበሽር ስርዓት እንዲመለስ የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ያም ሆነ ይህ ታዲያ የሀገሪቱ ሉኣላዊየሽግግር መንግስት ሊቀ መንበር በአብዮቱ 2ኛ ዓመት ላይ ትኩረት ያደረጉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል፡፡
የሀገሪቱ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ እና የሉኣላዊ ሽግግር ምክር ቤት ሊቀ መንበር አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን ፣የአልበሽር አገዛዝ የተወገደበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ሰራዊቱ በአብዮቱ የተገኙ ውጤቶችን እንደሚያስጠብቅ ፡፡
አል ቡርሃን በይፋዊው የትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ሱዳናውያንን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ሱዳናውያን ለመንግሥት ለውጥ ያበቃቸውን ተቃውሞ የጀመሩት በሰሜን ሱዳን በአትባራ ከተማ እ.ኤ.አ. ታህሳስ 19 ቀን 2018 ነበር፡፡ በወቅቱ የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ ወደ ሌሎች ከተሞች በፍጥነት የተስፋፋ ሲሆን መነሻውም የዳቦ ዋጋ መናር ነበር፡፡
ዛሬ በአብዮቱ ሁለተኛ ዓመትም ብዙም የለውጥ ፍሬ ያላዩት ሱዳናውያን በተለያዩ ስሜቶች አደባባይ ወጥተዋል፡፡