የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን የሀገሪቱን የክብር ሜዳይ ተሸለመ
በኳታሩ የአለም ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሱት የአትላስ አናብስቱ ትናንት ወደ ራባት ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል
የሀገሪቱ ንጉስም በቤተመንግስት ተቀብለው የክብር ሜዳይ ሽልማት አበርክተውላቸዋል
በኳታሩ የአለም ዋንጫ አስደናቂ ብቃትን ያሳየው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ትናንት ወደ ራባት ሲመለስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሞሮኳውያን አደባባይ ወጥተው በዶሃ አለምን ላስደመመው ብሄራዊ ቡድናቸው የጀግና አቀባበል አድርገዋል።
አሰልጣኝ ዋሊድ ሬግራጊ እና ተጫዋቾቻቸው በመዲናዋ በክፍት አውቶብስ እየተዘዋወሩ ከደጋፊዎች ጋር ፎቶ ሲነሱና ደስታቸው ሲጋሩ የሚያሳዩ መዋላቸውም ተነግሯል።
የአትላስ አናብስቱ በራባት ጎዳናዎች ተዘዋውረው ደስታቸውን ከህዝብ ጋር ከተጋሩ በኋላም በብሄራዊ ቤተመንግስት የክብር አቀባበል ጠብቋቸዋል።
ንጉስ ሞሃመድ ስድስተኛ፣ ልኡል አልጋወራሽ ሞላይ ኤል ሃሰን እና ልኡል ሞላይ ራሺድ በአሰልጣኝ ዋሊድ ሪግራጊ የተመራውን ብሄራዊ ቡድን አባላት ተቀብለዋል።
በኳታር አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ብሄራዊ ቡድን አባላት በሞሮኮ ትልቅ አብርክቶ ለሰጡ ሰዎች የሚሰጠውን የክብር ሜዳይም መሸለማቸውን ነው የሞሮኮ ብሄራዊ የዜና ወኪል የዘገበው።
የክብር ሜዳሉ ሲበረከት ከፈረንጆቹ 1963 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የቤልጂየም፣ ስፔን እና ፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድኖችን ከአለም ዋንጫው ያሰናበተው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን በፈረንሳይ ተሽንፎ ከፍጻሜው ውጭ ቢሆንም ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።
የአትላስ አናብስቱ በደረጃ ጨዋታውም በክሮሽያ ሽንፈትን ቢያስተናግዱም ለአፍሪካም ሆነ ለአረቡ አለም ኩራት የሆነ ብቃትን ማሳየት ችለዋል።
ብሄራዊ ቡድኑ ከፈረንሳይ ጋር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ካደረገ በኋላም ንጉስ ሞሃመድ ስድስተኛ ለዋሊድ ሬግራጊ ስልክ ደውለው ላሳዩት አስደናቂ ተጋድሎ ማመስገናቸው ተዘግቧል።
በዶሃ አራተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን ከአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለግማሽ ፍጻሜ በመድረስ አዲስ ታሪክ አጽፏል።