ኢትዮጵያ ከመጪው ጥቅምት ጀምሮ የግብጽ ኤምባሲዋን በጊዜያዊነት ልትዘጋ ነው
የኤምባሲው መዘጋት “ከህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም”ም ነው የተባለው
ኤምባሲው የሚዘጋው ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ ወጪ ለመቀነስ በሚል እንደሆነ እምባሳደር ማርቆስ ተናግረዋል
ኢትዮጵያ በካይሮ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ከጥቅምት ወር ጀምሮ በጊዜያዊነት እንደምትዘጋ በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ መናገራቸው ቢቢሲ አረብኛ ዘግቧል፡፡
ኤምባሲው ከሶስት እስከ ስድስት ወራት እንደሚዘጋ የተናገሩት አምባሳደሩ ዋና ምክንያቱ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአልጀርስ የሚገኘውን ኢምባሲዋን እንደምትዘጋ አስታወቀች
"ኤምባሲው አንዳንድ ወጪዎች ለመቀነስ በሚል ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሶስት እስከ ስድስት ወራት የሚዘጋ ይሆናል"ም ነው ያሉት አምባሳደሩ፡፡
አምባሳደሩ የኤምባሲው መዘጋት በሶስቱም ሀገራት ማለትም በኢትዮጵያ፣ግብጽ እና ሱዳን መካከል ካለው የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ጋር የሚገናኘው አንዳች ነገር እንደሌለም አስረድተዋል፡፡
ኤምባሲው ዝግ በሚሆንበት ወቅት የኤምባሲው ኮሚሽነር ጉዳዮቹን እንደሚከታተልም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ ወጪ ለመቀነስ በሚል ግብጽ፣ ካናዳ እና የባህረ ሰላጤ ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙትን ኤምባሲዎቿን በጊዜያዊነት እየዘጋች እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ከባህረ ሰለጤው ሀገራት በዩኤኢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቀጠናው ዋና የዲፕሎማቲክ ሚሽን ማእከል በመሆን አገልግሎቱ መስጠት እንደሚቀጥል ከዲፕሎማቲክ ምንጮቹ መረጃ ማግኘቱም አህራም ኦንላይን ዘግቧል፡፡
አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ እንደፈረንጆቹ ከነሃሴ 2020 ጀምሮ በካይሮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሞኑ በተለያዩ ሃገራት ለወከሏት አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች እና ሚሲዮኖች በሀገራዊ የለዉጥ እና የተቋም አደረጃጀት ስራዎች፣ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ስራ፣ አገራዊና አለም አቀፉዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ፣ዲጂታል ዲፕሎማሲ፣ የተሻሻለው የዉጭ ግንኘነት ፖሊሲ፣ የመረጃ ደህንነትና ስነ- ምግባር ጉዳዮች እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስልጠናን ስትሰጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡