የኪንሻሳው ስብሰባ በድርድሩ ወደ መቀራረብ ለመምጣት አዲስ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ታዛቢዎች ይገልጻሉ
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ አዲስ አበባ በምትገነባው የሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሦስትዮሽ የሚኒስትሮች ስብሰባን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡
በሀገሪቱ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ዛሬ ከሰዓት በኋላ የሕዳሴው ግድብ ድርድር እንደገና እንዲጀመር ለመወያየት የሦስቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ተጀምሯል፡፡
በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚካሔደው ድርድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ኪንሻሳ ያቀናው የሱዳን ልዑካን ቡድን ከአፍሪካ ህብረት ልዑካን ጋር በዝግ ስብሰባ አድርጓል፡፡
በሱዳን የመስኖ ሚኒስቴር አንድ ምንጭ ለአል ዐይን እንደገለፀው ፣ ሁለቱ አካላት በሕዳሴው ጉዳይ በኢትዮጵያ ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል አለመግባባት ባለባቸው ነጥቦች ዙሪያ መቀራረብ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ፌሊክስ ሼሲኬዲ የሚመራው አዲሱ የሦስትዮሽ ውይይት ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የሚኒስትሮችን ስብሰባ ለማዘጋጀት የሚካሔደው የቴክኒክ ባለሙያዎች ስብሰባ ቅዳሜ ዕለት ተደርጓል፡፡ እየተካሔደ ያለውን ስብሰባ በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡
ግብፅ እና ሱዳን ስምምነት ላይ ሳይደረስ የግድቡ ሁለተኛ ሙሌት እንዳይከናወን ቢጠይቁም ይግድቡ የውሃ ሙሌት ከግንባታው ጋር የተያያዘ መሆኑን የምትገልጸው ኢትዮጵያ በቀጣዩ ክረምት ሙሊቱን ለማከናወን ዝግጅት በማድረግ ላይ ናት፡፡
ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ ፣ አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታትም በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ በሱዳን የቀረበውን ሀሳብ ግብፅ የደገፈች ሲሆን ኢትዮጵያ አልተቀበለችውም፡፡ ባለፈው ሳምንት የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ “ከግብጽ ውሃ ማንም አንዲትም ጠብታ ሊነካ አይችልም ፤ ይህ ከሆነ ግን ማንም ሊያስበው የማይችል አለመረጋጋት በቀጣናው (ምስራቅ አፍሪካ) ይፈጠራል” በማለት መዛታቸው ይታወሳል፡፡
ለፕሬዝደንቱ ዛቻ ምላሽ ያልሰጠችው ኢትዮጵያ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እንደሚከናወን በተደጋጋሚ በተለያዩ ባለስልጣናቶቿ አሳውቃለች፡፡
ታዛቢዎች የኪንሻሳው ስብሰባ የሕዳሴ ግድብ ድርድርን ወደ መቀራረብ መንገድ ለማምጣት አዲስ አጋጣሚ አድርገው ይመለከታሉ፡፡