የሕዳሴ ግድብ ውይይት ቅዳሜ እለት በኪንሻሳ ይጀምራል
ውይይቱን የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር እና የዲአር ኮንጎ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ቺሲኬዲ ይመሩታል
የግብፅ ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመጪው ቅዳሜ በኪንሻሳ ይገናኛሉ
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለስልጣናት እንዳሉት የግብፅ ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በመጪው ቅዳሜ በኪንሻሳ ተገናኝተው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ያደርጋሉ ፡፡
የኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ለሦስት ቀናት የሚካሄደውን ስብሰባ ባለፈው ወር የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን የተረከቡት ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቺሲኬዲ ይመሩታል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በውይይቱ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡
ላለፉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያ ፣ ግብፅ እና ሱዳን አዲስ አበባ እየገነባች ባለው የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ሲደራደሩ ቢቆዩም ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በቀጣዩ ክረምት እንደምታከናውን አስታውቃለች፡፡ ለዚህም የደን ምንጣሮ ለማካሔድ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
በሌላ በኩል ግብፅ እና ሱዳን በቅርቡ ካደረጉት የወታደራዊ ስምምነት በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ዛቻ አዘል መልዕክቶችን ማስተላለፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ የግብፁ ፕሬዝደንትአብዱል ፈታህ አል ሲሲ ከቀናት በፊት ባደረጉት ንግግር “ከግብፅ ውሃ ማንም አንዲትም ጠብታ ሊነካ አይችልም” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን ፣ አክለውም “ይህ ከሆነ ግን ማንም ሊያስበው የማይችል አለመረጋጋት በቀጣናው (ምስራቅ አፍሪካ) ይፈጠራል” ብለዋል፡፡
የፕሬዝደንቱን ንግግር ተከትሎ በርካታ የአረብ ሀገራት ባወጡት መግለጫ በግድቡ ጉዳይ ከግብፅ ጎን እንደሚቆሙ ያሳወቁ ሲሆን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በበኩሏ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን መፍትሄ ለማምጣት ድርድሩ እንዲቀጥል ጠይቃ ፣ ለዚህም ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ቃል አቀባይ ሳሙኤል ዋርበርግ ባወጡት መግለጫ “በሕዳሴ ግድብ ልዩነት ውስጥ ያሉ ወገኖች በድርድር መፍትሄ ላይ እንዲደርሱ እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡
የዓባይ ወንዝ ለግብፅ ፣ ለሱዳንና ለኢትዮጵያ ህዝቦች ያለውን ጠቀሜታ ተገንዝበን ለሕዳሴ ግድብ ችግር ሰላማዊ መፍትሄ ለማምጣት ማንኛውንም እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ ነን ሲሉም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡