የግብፅ የውጭ ጉዳይ እና የውሃና መስኖ ሚኒስትሮች ካርቱም ናቸው
ሚኒስትሮቹ ከሌተናል ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና ከጠ/ሚ አብደላ ሀምዶክ ጋር ይወያያሉ ተብሏል
በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር ለመምከር ነው ሚኒስትሮቹ ካርቱም የገቡት
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ እና የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ሞሃመድ አብደል አቲ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር ለመመካር ካርቱም ገብተዋል።
አል ዐይን ኒውስ ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሚኒስትሮቹ ካርቱም ሲደርሱ የሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃና መስኖ ሚኒስትሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በካርቱም በሚኖራቸው ቆይታም ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለው የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ትኩረት አድርገው ይመክራሉ ነው ተባለው።
ሚኒስትሮቹ በካርቱም ቆይታቸው ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር እንደሚመክሩም ተነግሯል።
ካይሮ እና ካርቱም ፣ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ከማከናወኗ በፊት አስገዳጅ ስምምነት ላይ እንዲደረስ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ቀጥለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መቃረቡን ተከትሎ ፣ ሁለቱም ሀገራት አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ ያላቸውን አቋም በማንጸባረቅ ላይ ይገኛሉ።
ሱዳን ባሳለፍነው ሳምንት የጋራ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መካሄድ የለበትም ፤ ካልሆነ ብሔራዊ ደህንነቴን ለመጠበቅ ሁሉንም ህጋዊ መንገዶች እጠቀማለሁ ማለቷ ይታወሳል። ግብፅም እንዲሁ በተደጋጋሚ ዛቻ አዘል መልዕክቶችን ከፕሬዝደንቷ ጀምሮ በተለያዩ ባለስልጣናቷ በኩል አስተላልፋለች፡፡
ሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ የገለጸችው ኢትዮጵያ ፣ አስገዳጅ ስምምነት የመፈረም ፍላጎት የላትም ፤ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም በተያዘው ጊዜ እንደምታከናውን ቁርጠኛ አቋም ይዛለች፡፡