ፌስቡክ ኢትዮጵያን ዒላማ አድርገው መረጃ ሲያሰራጩ የነበሩ የግብፅ ገጾችን ዘጋ
ገጾቹ አማርኛ ቋንቋን በመጠቀም የህዳሴ ግድብ የሚተቹና ሀሰተኛ መረጃዎችን ያሰራጫሉ
የፌስቡክ ኩባንያ የዘጋቸው ገጾች በድምሩ ከ300 ሺህ በላይ ተከታዮች ያላቸው ናቸው
ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ፌስቡክ መቀመጫቸውን ግብፅ ያደረጉ እና ኢትዮጵያን ኢላማ ያደረጉ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ገጾችን መዝጋቱን አስታወቀ።
ኩባንያው “17 የፌስቡክ አካውንቶችን፣ ስድስት የፌስቡክ ገጾችን እንዲሁም ሶስት የኢንስታግራም ገጾችን ዘግተናል” ሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የፌስቡክ ኩባንያ ባደረገው ምርመራ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ገጾቹ መቀመጫውን ግብፅ ያደረገ “ቢ ኢንተራክቲቭ” የተባለ ማርኬቲንግ ኩባንያ አካል ሆነው መገኘታቸውንም አስታውቋል።
የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ገጾቹ የፌስቡክን የውጭ ጣልቃ ገብነት ፖሊሲ የሚጥሱ ሆነው መገኘታቸውን እና ትክክለኛ ያልሆነ መረጃን በተቀናጀ መልኩ የሚያሰራጩ ናቸው።
የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ገጾቹ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት በሚነገረውን አማርኛ ቋንቋን በመጠቀም መረጃዎችን እንደሚያሰራጩም ኩባንያው አስታውቋል።
ገጾቹ አማርኛ ቋንቋን በመጠቀም ከሚያሰራጩት መረጃዎች ውስጥም ኢትዮጵያ እየገነባች የሚገኘውን ህዳሴ ግድብ የሚተቹ መሆናቸውንም ፌስቡክ ገልጿል።
የፌስቡክ ኩባንያ የዘጋቸው ገጾች በድምሩ ከ300 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሏቸው ሲሆን፤ ከኢትዮጵያም በተወሰነ መልኩ የሰዎችን ተሳትፎ ማግኘት ጀምረው ነበረ።
በተጨማሪም የፌስቡክ ኩባንያ በአልባንያ፣ ስፔን፣ ኢራን፣ አርጀንቲና፣ ኤልሳልቫዶር፣ እስራኤል፣ ቤኒን ኮሞሮስ፣ ጆርጂያ፣ ሜክሲኮ የሚገኙ በርካታ የፌስቡክ ገጾችን መዝጋቱም ተነግሯል።
በዚህም መስረት በአጠቃላይ 1 ሺህ 167 የፌስቡክ አካውንቶችን፣ 255 የፌስቡክ ገጾችን ፣ 34 የፌስቡክ ግሩፖችን እንዲሁም 290 የኢንስታግራም ገጾችን ነው የዘጋው።