የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም 110 ንጹሃን ሰዎች መግደላቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ
70 ሰዎች መንገድ ላይ እያሉ፤ 40 ሰዎች ደግሞ ቤታቸው ውስጥና ከቤታቸው እንደወጡ በማድረግ ተገድለዋል ብሏል አቃቤ ህግ
አቃቤ ህግ በአስገድዶ መድፈርና በንጹሃን ግድያ ተሳትፈዋል ያላቸውን 53 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይም ክስ መስርቷል
በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ህዳር 19 እና 20፣ 2013 ዓ.ም በነበረው ውጊያ የኤርትራ ወታደሮች 110 ንጹሃን ሰዎች መግደላቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባውጣው የምርመራ ሪፖርት አስታወቋል፡፡
አቃቤ ህግ በትናትናው እለት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን ምርመራ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫው በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ህዳር 2013 ዓ.ም ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎች ላይ የምርመር ስራ መቀጠሉን አስታውቋል።
እስካሁን ባደረገው ምርመራም አክሱም ከተማ ህዳር 19 እና 20፣ 2013 ዓ.ም በነበረው ውጊያ 110 ንጹሃን ሰዎች በኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን አረጋግጧል።
በምርመራው መሰረትም 70 ሰዎች በአክሱም ከተማ ውስጥ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ መንገድ ላይ እያሉ መገደላቸውን ያመላከተው ምረመራው፤ ከሟቾቹ ውስጥም ወታደራዊ የደንብ ልብስ ባይለብሱም በጦርነቱ የተሳተፉ ሰዎች መኖራቸው መረጋገጡን አስታውቋል።
በሌላ መልኩ 40 ንጹሃን ሰዎች ደግሞ የኤርትራ ወታደሮች ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሰሳ ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርገው እና በቤታቸው ውስጥ መገደላቸውንም ምርመራው አመላክቷል።
ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ በርከት ያሉ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት መድረሱን ያመላከተው ጠቅላይ አቀቤ ህግ ሪፖርት፤ ከእነዚህም ውስጥ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች፣ ቅድስት ማርያም ሆስፒታል ብራና ሆቴል ይገኙበታልም ብሏል።
በወቅቱ በአክሱም በነበረው ውጊያ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት 119 ሰዎች የምስክርነት ቃል እንዲሰጡ መደረጉን፣ የህክምና ማስረጃዎች፣ የፎቶ እና ቪዲዮ ማስረጃዎችን ማሰባሰቡንም ጠቅላይ አቃቤ ህግ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡
በተመድ የኤርትራ አምበሳደር ሶፊያ ተስፋማርያም በሚያዚያ ወር መጨረሻ ለተመድ በጻፊት ደብዳቤ የኤርትራ ጦር በትግራይ ግጭት መሳተፉን አምነው፤ጦሩ በአስገድዶ መድረርና ጾታ ጥቃት ተሳፏል የሚለውን የተመድ ሪፖርት ሀሰት ነው ሲሉ አስተባብለው ነበር፡፡
አምባሳደሯ "አንዣቦ የነበረው ስጋት በአብዛኛው በመወገዱ ኤርትራና ኢትዮጵያ የኤርትራ ኃይሎችን ለማስወጣትና የኢትዮጵያ ሠራዊት በድንበር ላይ እንዲሰማራ ለማድረግ በከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው አማካይነት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል" ብለው መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ቀደም ብሎው ወደ ኤርትራ አቅንተው በነበረበት ወቅት ኤርትራ ጦር ለማስወጣት መስማማታቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
በኢትዮጵያውያን ወታደሮች ስለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች የአቃቤ ህግ ሪፖርት
ጠቅላይ አቃቤ ህግ በትግራይ ክልል በንጹሃን ግድያና በጾታ ጥቃት ላይ ትኩረት በማድረግ ባካሄደው ምርመራ፣ የወታደራዊ ግዴታ በሌለበት ወቅት በግድያ የተጠረጠሩ 28 የኢትዮጵያ ወታሮች ላይ ክስ መመስረቱን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ጾታ ጥቃትና አስገድዶ መድፈር የፈጸሙ 25 ወታደሮችም ክስ ተመስርቶባቸዋል ብሏል አቃቤ ህግ፡፡ በክሶቹ ላይ በአጭር ጊዜ ፍድድ እንደሚሰጥ አቃቤ ህግ ገልጿል፡፡
በትግራይ ክልል ውስጥ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ክልሉን ሲመሩ የነበሩ የህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ጦር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር።
በክልሉ ግጭቱን ተከትሎ የንጹሃን ግድያና ፆታዊ ጥቃት ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰት በግጭቱ ተሳታፊ ሃይሎች መፈጸማቻን በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ)ና በተለያዩ የአለምአቀፍ የመብት ድርጅቶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መጥቀሱ ይታወሳል፡፡