የተባበሩት መንግስታት የተመሰረተበት 75ኛ ዓመት እየተከበረ ነው
ዓለም የተጋረጠባትን ፈተና ለመቋቋም የጋራ ጥረት ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንስተዋል
ጠ/ሚ ዐቢይ በቪዲዮ ንግግራቸው ኢትዮጵያ ተዓማኒ ምርጫ እንደምታደርግና ለተመድ ተልዕኮዎች ስኬት እንደምትቆም ተናግረዋል
የተባበሩት መንግስታት የተመሰረተበት 75ኛ ዓመት እየተከበረ ነው
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ መሰል ጦርነቶችን ለመከላከል በአውሮፓውያኑ 1945 የተመሰረተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 75ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ ነው፡፡
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የድርጅቱ 75ኛ ዓመት ክብረ በዓል በአብዛኛው በቪዲዮ በመታገዝ የአባል ሀገራትን ተወካዮች ከያሉበት በማሳተፍ ነው የሚካሔደው፡፡
የክብረ በዓሉ መሪ ሀሳብ “ለምንፈልገው መጪው ጊዜ ፣ የምንፈልገው የተባበሩት መንግስታት” “The future we want, the United Nations we need” የሚል ሲሆን በወጣቶች ሚና ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የተባበሩት መንግስታት ለመጪው ትውልድ ጠቃሚ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ ዓላማው ነው፡፡
የፊት መሸፈኛ ጭምብሎችን ለብሰው በርቀት ተለያይተው ከ 193 አባል ሀገራት የተውጣጡ አንድ ወይም ሁለት ዲፕሎማቶች በተባበሩት መንግስታት መቀመጫ ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው አጠቃላይ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንደተገኙ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ጽፏል፡፡
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና ሌሎች የተባበሩት መንግስታት ባለሥልጣናት ከመድረኩ ንግግር ሲያደርጉ ፣ ሌሎች ሁሉም የአባል ሀገራት መሪዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቶቻቸውን በተዘጋጁ ቪዲዮዎች አማካኝነት አቅርበዋል፡፡
አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባደረጉት ንግግር ለዓለማችን ዉስብስብ ችግሮች የሀገራት ብሔራዊ ሉዓላዊነት በተጠበቀ መልኩ ሁሉንም ያሳተፈ የጋራ መፍትሔ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ መስራች እና አባል ከሆኑ ሀገራት አንዷ የሆነችው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም በቪዲዮ ንግግር አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር የተባበሩት መንግስታት መስራች አባቶች ቀጣዩን ትውልድ ከጦርነት የመታደግ እና የዓለም ህዝብ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር ራዕይ ማንገባቸውን አንስተዋል፡፡ በዚህ ራዕይ መሰረት ድርጅቱ ዓለምን ከአስከፊ የዓለም ጦርነት ከመታደግ ባለፈ በሰብዓዊ ድጋፍ ረገድም ብዙ መስራቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አንስተዋል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ ድርጅቱ ብዙ ፈተናዎች እየገጠሙት ዓለምም ስጋቷ እየተባባሰ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ የጋራ አመራር እና ጥረት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡ “አፍሪካም በቂ ዉክልና ሊኖራት ይገባል” ብለዋል፡፡ በኮቪድ-19 ምክንያት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚደረገው ጥረት መቀዛቀዝ ማሳየቱን በመጥስ አፍሪካ በተለያየ መስክ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት አንስተዋል፡፡ የትኛውም ሀገር ዓለም አቀፍ ፈተናን ብቻውን መወጣት አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለነዚህ ፈተናዎች የጋራ መፍትሔ ብቻ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተመድ መስራች አባል እንደመሆኗ በጋራ ደህንነት እና ጥረት እንደምታምንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡ በድርጅቱ የሰላም ተልዕኮ ኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት ድጋፍ በማድረጓ ኩራት እንደሚሰማትም ነው የተናገሩት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ሰብዓዊ መብት ጥበቃ በሪፎርሙ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ እንዲሁም ሰላመዊ እና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማድረግ መንግስታቸው ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ከተያዙ የ 84 የሀገራት መሪዎች ወይም መንግስታት መካከል የመጀመሪያው ተራ ቁጥር ላይ ተይዘው የነበሩት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ንግግር አለማድረጋቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ከዛሬ መስከረም 12/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 19 በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ክርክሮችን እንደሚያደርግ ከድርጅቱ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡