የሱዳን መንግስት እና የኤስ.ፒ.ኤል.ኤም የጁባ ድርድር በልዩነቶች ታጅቦ እንደቀጠለ ነው
ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም በሱዳን ያልተማከለ የመንግስት አወቃቀር እንዲኖር አጥብቆ እንሚፈልግ የአል-ዐይን ምንጮች ተናግረዋል
የሱዳን መንግስት በሀገሪቱ ክልሎች ከህዝበ ውሳኔ ጋር የተያያዘ የሚነሱ ሀሳቦችን መስማት እንደማይፈልግ ተገልጿል
በሱዳን መንግስት እና የሱዳን ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ/ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም/ መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ድርድር አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በጁባ እየተካሄደ የሚገኘውና በውስጥ የተለያዩ የስምምነት ማእቀፎችን ያካተተው ድርድር እስከ ነገ እንደሚቀጥልም ነው የድርድሩ ቃል አቀባይ ሆነው የተሰየሙት ካሊድ ኦማር የተናገሩት፡፡
የድርድሩ ቃል አቀባይ የጁባው ድርድር እንደሚቀጥል ቢናገሩም፣ እሳቸው ግን ድረድሩ ሳያልቅ በዛሬው ዕለት ካርቱም ተገኝተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ድርድሩ ሳያልቅ ወደ ሱዳን የተመለሱበትን ምክንያት በተመለከተ ከአል-ዐይን ለቀረበላቸው ጥያቄ “የእሳቸውና የሱዳን ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ቡታንያ ዲናር ወደ ካርቱም መመለስ በድረድሩ ላይ የሚፈጥረው ምንም ዓይነት ተጽእኖ እንደሌለው” ገልጸዋል፡፡ እነርሱ የተመለሱት ለሌላ ስራ መሆኑን ገልጸው ቀሪ የመንግስት ልዑካን በጁባ መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ቃል አቀባዩ ካሊድ ኦማር ይህን ይበሉ እንጂ “በጁባ በመካሄድ ላይ ያለውና በዓብዱል አዚዝ አል-ሂሉ የሚመራው ድረድር ከስምምነቶች ባሻገር በልዩነቶችም ጭምር የታጀበ” መሆኑን የአል-ዐይን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
እንደ አል-ዐይን ምንጮች ከሆነ የጁባው ተደራዳሪ አካላት በ19 ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ከስምምነት ላይ እስኪደርሱ ድርድሩ የሚራዘምበት እድል ሰፊ ነው፡፡
“ከወሰን ማካለል በሻገር በኤስ.ፒ.ኤል.ኤም በኩል የሚጠቀሱት ግዛቶች (የኑባ እና የጥቁር ዓባይ ኮርዶፋንና ፉንጅ) ህዝበ-ውሳኔ ጉዳይ ተደራዳሪ ኃይሎቹ የማይስማሙባቸው አበይት ነጥቦች ናቸው” ሲሉም ነው ስማችን እንዳይጠቀስ ያሉት የአል-ዐይን ምንጭ የተናገሩት፡፡
የሱዳን መንግስት “በፍላጎት ላይ የተሞረከዘ አንድነት” በሚል የቀረበው ሀሳብ፣ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን”ን የሚያመለክት በመሆኑ “በፍፁም አልቀበለውም” ማለቱም ነው የተገለጸው፡፡
ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም በበኩሉ መንግስት ከሚለው የተማከለ የአስተዳደር ስርዓት በተቃራኒ ያልተማከለ የመንግስት አወቃቀር እንዲኖር ይፈልጋል፡፡
በድርድሩ የሱዳን መንግስት ተወካዮች፣ የደቡብ ሱዳንን አይነት የመገንጠል ታሪክ እንዳይደገም በመስጋት ከ “ኑባ እና ፉንጅ ህዝበ-ውሳኔ” ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ሀሳብ አልፈልግም ማለታቸውንም ነው የምንጮቻችን መረጃ የሚያመለክተው፡፡
ኤስ.ፒ.ኤል.ኤም የመንግስት ስርዓቱ ፕሬዝደንታዊ እንዲሆን ፍላጎት ሲኖረው መንግስት በበኩሉ ጉዳዩ በህገ-መንግስታዊ ጉባኤ የሚወሰን መሆኑን አስታውቋል፡፡