“ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት የጀመረችውን ጉዞ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ያስቁምልን” ሲሉ ግብፅ እና ሱዳን ጠየቁ
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብፅ እና ሱዳን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል
ሁለቱ ሀገራት “የኢትዮጵያ ፖሊሲ የሚያስከትለውን አደጋ ለመከላከል የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ንቁ ጣልቃ ይግባ” ብለዋል
የግብፅ የውጭ ጉዳይ እና መስኖ ሚኒስትሮች በሱዳን ባደረጉት የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት ፣ ከሱዳን አቻዎቻቸው ጋር መገናኘታቸውን ተከትሎ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የሕዳሴ ግድቡን ጉዳይ በተመለከተ ሁለገብ ስምምነት ላይ ለመድረስ “ኢትዮጵያ በቁም ነገር ፣ በታማኝነት እና በእውነተኛ የፖለቲካ ፍላጎት እንድትደራደር በቀጣና ፣ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ ደረጃዎች ግፊት እንዲደረግ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እንደሚሰሩ” አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በሕዳሴው ግድብ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ “ፍትሃዊ እና ህጋዊ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ እንደሚሰሩ” ገልጸዋል፡፡
በቀጠናው እና በአፍሪካ አህጉር ፀጥታ ፣ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስጠበቅ ፣ “የግብፅ እና የሱዳን ቅንጅት አስፈላጊነት” ላይ መስማማታቸውንም የሚያትተው መግለጫው ፣ ለዚህም “ኢትዮጵያ በግድቡ ጉዳይ የያዘችውን ፖሊሲ መቀጠሏ የሚያስከትለውን አደጋ ለመከላከል የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ንቁ ጣልቃ ገብነትን ይጠይቃል” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በመጪው የክረምት ወቅት “የሕዳሴውን ግድብ ለመሙላት የጀመረችውን ጉዞ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ እንዲያስቆም” ነው በመግለጫቸው የጠየቁት፡፡
አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ማከናወን እንደሚያሰጋቸውም ሁለቱ ሀገራት በድጋሚ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት በተደጋጋሚ የገለጸችው ኢትዮጵያ ፣ አስገዳጅ ስምምነት የመፈረም ፍላጎት የላትም ፤ የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም በተያዘው ጊዜ እንደምታከናውን ቁርጠኛ አቋም ይዛለች፡፡