ሃገራቱ በሚወሰኑበት ድንበር አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር የማርገብ ዓላማ ሊኖረው እንደሚችል ተገምቷል
አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ ረፋድ አስመራ ገብተዋል
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን ለአንድ ቀን ይፋዊ ስራ ጉብኝት ዛሬ ረፋድ አስመራ መግባታቸውን የኤርትራ የመረጃ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል፡፡
አል ቡርሃን እና ልዑካቸው አስመራ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱ ጊዜ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የኤርትራ ባለስልጣናት አቀባበል እንዳደረጉላቸውም ነው ሚኒስትሩ ያስታወቁት፡፡
መሪዎቹ በሁለትዮሽ እና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩም ገልጸዋል፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ ሃምሌ ከፍተኛ የኤርትራ የመከላከያ ኃላፊዎች ወደ ካርቱም አቅንተው ከምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሃምዳን ደገሎ (ሄሜቲ) ጋር መምከራቸው ይታወሳል፡፡
የአል ቡርሃን የኤርትራ ጉብኝት ለምን?
በጉብኝቱ የሁለትዮሽ የተባሉትን ግንኙነቶች ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡
በተለይም የድንበር አካባቢ የጸጥታና ደህንነት ጉዳይ ቀዳሚ የውይይት አጀንዳ ሊሆን እንደሚችልም ነው ለሃገራቱ ፖለቲካ ቅርበት ያላቸው የመረጃ ምንጮች ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት፡፡
ኤርትራ ከሱዳን ጋር በቀይ ባህር እና በምስራቃዊ ሱዳን የከሰላ ክልል አካባቢዎች ትዋሰናለች፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የንግድና የሰው እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው መሆኑን ተከትሎም በወሳኝ የድንበር አካባቢነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሆኖም ተደጋጋሚ ግጭቶች አያጧቸውም፡፡ ግጭቶቹ በአካባቢው ካለው የብሄርና ሌሎችም ጥያቄዎች ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡
የሽግግር ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ጉብኝትም ይህንኑ ለማጠናከር የሚያስችል ነው እንደ የመረጃ ምንጮቹ ገለጻ፡፡ የብሄር ጉዳይ ለተጫናቸው ግጭቶች መላ መዘየድ የጉብኝቱ አካል ሊሆን እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡
የብሄር ጉዳይ እንዴት?
በምስራቃዊ ሱዳን የሚገኘው የከሰላ ክልል ተሰነይ ተብሎ ከሚጠራውና ሃገራቱ ከሚጎራበቱበት ድንበር በ45 ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ ከሚገኘው የኤርትራ አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ በንግድ ከተማነቱ የሚታወቅም ሲሆን በአትክልትና ፍራፍሬ አምራችነቱ ይጠቀሳል፡፡
ከ7 ገደማ የበጃ ጎሳዎች መካከል የሆኑት የሃደንደዋ እና የቤኒዓምር ጎሳዎችም ከሌሎች ብሄሮች ጋር በመሆን በከሰላ ይኖራሉ፡፡ የሃደንደዋ ጎሳዎች ከፍተኛ ቁጥር አላቸው፡፡ በከፍተኛ የክልሉ የኃላፊነት ደረጃም ላይ ይገኛሉ፡፡
የቤኒዓምር ጎሳዎች ደግሞ በዋናነት ጋሽ-ባርካ ተብሎ በሚጠራው የኤርትራ ክልል ነው የሚገኙት፡፡ ቋንቋቸውም ከትግረ ቀጥሎ በስፋት ይነገራል፡፡ ከፍተኛ የነዋሪዎች ቁጥር ያለው ጋሽ-ባርካ በከፍተኛ አምራችነቱም ይታወቃል፡፡ የኤርትራ የዳቦ ቅርጫት በመባልም ነው የሚታወቀው፡፡
ሆኖም በሁለቱም ጎሳዎች መካከል ዓመታትን የተሻገረ መናቆር አለ፡፡ ራሳቸውን በ“ነባር ህዝብ”ነት የሚጠቅሱት የሃደንደዋ ጎሳዎች ቤኒዓምሮችን በ“መጤ”ነት ይከሳሉ፡፡ ከቀይ ባህር ጀምሮ አካባቢውን ማስተዳደር አለብን በሚል የሚያቀርቡት የስልጣን ጥያቄም ለተደጋጋሙ አካባቢያዊ ግጭቶች መነሻ እንደሚሆንም ይነገራል፡፡
የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር ሃሰን አልበሽር ይህንን ልዩነት ለፖለቲካ ፍጆታ ይጠቀሙበት እንደነበርም ነው አንደኛው የአል ዐይን ምንጭ የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክም በነዚሁ ጥያቄዎች ምክንያት ከቀናት በፊት ከፍተኛ ተቃውሞን አስተናግደዋል፡፡
ክልሉን እንዲያስተዳድር የሾሙት አዲስ ባለስልጣን ከወደ ቤኒዓምር ጎሳመሆኑ በሃደንደዋ ጎሳዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ ቁጣውን ተከትሎ በተቀሰቀሰ ግጭትም የሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከፍተኛ የንብረት ውድመትም ደርሷል፡፡ ይህ የሆነው ከአስር ቀናት በፊት ነው፡፡
የአል ቡርሃን የአስመራ ጉብኝት ቅቡልነት ካጣው ሹመት ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰውን ግጭት ከማርገብ በዘለለ የድንበር አካባቢውን ሰላም የማረጋገጥ ተልዕኮ እንደሚኖረውም ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡ ኤርትራ ግጭቱን ለመቆጣጠር የሚያስችል ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳላትም ጠቁመዋል፡፡