ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የሱዳን የሽግግር መንግሥት የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ካርቱም ተገኝተዋል
ኢትዮጵያና ሱዳን በአጋርነት መቆማቸውን እንደሚቀጥሉ ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሱዳን የሽግግር መንግሥት የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት ክብረ በዓል ተከትሎ በካርቱም ተገኝተው ከሱዳን አቻቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡
በሁለትዮሽ ውይይቱ ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እስካሁን ድረስ የሱዳን መንግሥት በስኬት ያጠናቀቃቸውን ምዕራፎች እንዲሁም የፖለቲካ ውይይቶች በቀጣይነት መከናወናቸውን አድንቀዋል። የኢትዮጵያ እና የሱዳንን ግንኙነትም አስመልክተው፣ የሁለቱ ሀገራት ዕጣ የተሳሰረ መሆኑን እና የተመሰረተውም ለረዥም ጊዜ በዘለቀው ታሪካዊ እና ስትራተጂያዊ ግንኙነት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። “አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሀገር ነን” በማለት አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፣ የሕዳሴውን ግድብ እና የድንበር ማካለል ሥራን ጨምሮ የትኛውም ጉዳይ ቀጣይነት ባለው እና በመተማመን ላይ በተመሰረተ ውይይት አማካኝነት እንደሚፈታ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክም በበኩላቸው፣ የሁለቱ ሀገራት ተመጋጋቢ ተፈጥሮ ለጋራ ጥቅም በትብብር እንዲሰሩ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል። በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ትሥሥር በማጠናከር የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚ ማሳደጋቸው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን እንዲሁም አፍሪካን በኢኮኖሚ የማነቃቃት ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ሁለቱም አካላት አንዳቸው የአንዳቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ በአጋርነት መቆማቸውን እንደሚቀጥሉ እና ማንኛውንም ጉዳይ በቀጣይ ውይይት እና ድርድር እንደሚፈቱ ማረጋገጣቸውን የጠ/ሚ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር ከስልጣን ከተነሱ 16 ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁንና ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን ከተነሱ ወዲህም ቢሆን የሀገሪቱ ችግር ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ በተለይም ሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀቀውስ ዉስጥ የገባች ሲሆን ከችግሯ ለመውጣት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በመማጸን ላይ ነች፡፡