
አስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸመው ተከሳሽ በእስራት ተቀጣ
ተከሳሽ ዳግም ሚኪ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታው አሰሙ ድልድይ ተብሎ በሚጠራዉ አካባቢ መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 620/2/ሀ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ በፈፀመው 18 ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ የሚፈፀም የግብረ ስጋ ድፍረት በደል ወንጀል ተከሶ ነው ፍርድ ቤት የቀረበው፡፡
የክስ ዝርዝሩ እንደሚያስረዳው የ15 ዓመት ታዳጊ የሆነችው የግል ተበዳይ ከላይ በተጠቀሰው ቀን ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት አካባቢ ዳቦ ለመግዛት ከቤት ወጥታ ስትሄድ ተከሳሽ ከኋላ በኩል በመምጣት አፏን አፍኖ በጩቤ በማስፈራራት ወደ ጨለማ ቦታ አስገብቶ አስገድዶ የደፈራት እና ክብረ ንፅህናዋን የገረሰሰ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ ክስ መሰርቶበታል፡፡
ተከሳሽ ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለት የዕምነት ክህደት ቃሉን የሰጠ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ያስረዳሉ ያላቸውን የሰው እና የሰነድ ማረጃዎች በማቅረብ ተከራክሯል፡፡
ተከሳሽም በበኩሉ መከላከያ ምስክር ያቀረበ ቢሆንም ድርጊቱን ስላለመፈፀሙ ማስረዳት ባለመቻላቸው የግራ ቀኙን ክርክር ሲያደምጥ የነበረው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎት ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሹ በሰባት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል ሲል የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አስነብቧል ፡፡