
ለመሆኑ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የትኞቹን የትስስር ገጾች ይጠቀማል?
የማህበረሰብ ትስስር ገጾች እና ኢትዮጵያ
በማህበረሰባዊ የትስስር ገጾች የመገልገሉ ነገር እያደገ መጥቷል፡፡የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም አድጓል፡፡ በተለይ የተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) ተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱ የማህበራዊ የትስስር ገጾች ተጠቃሚውን ቁጥር በዚያው ልክ ከፍ እንዳደረገው ነው የሚነገረው፡፡
እንደ ኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ከሆነ በኢትዮጵያ 43 ሚሊዬን ዜጎች ሞባይል ይጠቀማሉ፡፡ ከነዚህ መካከልም 22 ሚሊዬን ገደማው በይነ መረብን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ ብዙዎቹ ፌስቡክን መሰል ማህበረሰባዊ የትስስር ገጾችን መጠቀም ያዘወትራሉ፡፡
ለመሆኑ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የትኞቹን የትስስር ገጾች ይጠቀማል?
ፌስቡክ በብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የትስስር ገጾች ተጠቃሚ ዘንድ እንደሚዘወተር ይነገራል፡፡ከሌሎቹ የተሻለ የተገልጋይ ቁጥርም አለው፡፡ መቀመጫውን አየርላንድ ደብሊን ያደረገውን የገጸ ድር ሁኔታዎችን በተተነተኑ መረጃዎች ተደግፎ የሚያጠናው ስታት ካውንተር (Stat Counter) የተሰኘ ተቋም መረጃም ይህንኑ ያመለክታል፡፡
በዓለም አቀፍ የመረጃ ዝርዝሩ ውስጥ የኢትዮጵያ ነው በሚል ባስቀመጠው መረጃ መሰረትም እስከያዝነው ወርሃ ጥር ባጠናቀረው መረጃ መሰረት 90 በመቶው የሞባይልም ሆነ የተለያዩ ኮምፒውተሮች ተጠቃሚ ፌስቡክን የሚገለገል ነው፡፡ 3 ነጥብ18 በመቶ ዩቲዩብን፣ 2 ነጥብ 96 በመቶው ትዊተርን ይጠቀማሉ፡፡ የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ደግሞ ከ1 በመቶ በታች (0.27 በመቶ) ናቸው፡፡
ፌስቡክን የሚገለገሉ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦችም በርካታ ተከታዮችን ለማፍራት ችለዋል፡፡በተለይም ዜና ነክ መረጃዎችን በተለያዩ መልኮች ለማድረስ የሚሞክሩ ገጾች፣ታዋቂ ሰዎች፣አክቲቪስቶች እና ሌሎችም በርካታ ተከታዮች አሏቸው፡፡ በሰውሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ) እንደሚታገዝ የሚነገርለት ዓለምአቀፉ የማህበራዊ ሚዲያ ግብይት ተቋም ሶሻል ቤከርስ (social bakers)
1. Tewnet.com
2. Mereja.com እና
3. DireTube
ከ3 ሚሊዬን በላይ ተከታይ ያላቸው ቀዳሚ የዜና ነክ መረጃ የፌስቡክ ገጾች መሆናቸውንም አስቀምጧል፡፡