ስምንት የአፍሪካ ሀገራት ለኢትዮጵያ የሳተላይት ምስል ግዢ ጥያቄ አቀረቡ
ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት ሳተላይት ማምጠቋን ተከትሎ ለሀገሪቱ የሳተላይት ምስል ግዢ ጥያቄ እየቀረበ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ የሳተላይት ምስል ሽያጩን በራሷ መመሪያ መሠረት ከገዢ ሀገራት ጋር ውል በመፈፀም መሸጥ እንደምትጀምር የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንሰቲቲዩት ይፋ አድርጓል።
የህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት የሰው ሃብትና ቴክሎጂ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንሰቲትዩት የሳተላይቷን ቁጥጥርና መረጃ አሰባሰብ ዛሬ ታህሳስ 13 ቀን 2012 ዓ.ም ተመልክተዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራቸውን በማኖራቸው የኢንስቲትዩቱን ሰራተኞች አመስግነዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ኢትዮጵያን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ባለብዙ ተልዕኮ የሳተላይት መረጃ መቀበያ ተከላ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።
የመቀበያ አንቴናው ሀምሳ ሴንቲ ሜትር የምስል ጥራት እና እስከ አምስት የሚደርሱ የሳተላይቶችን መረጃ በአንድ ጊዜ መቀበል የሚያስችል ነው።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንሰቲትዩት ዳይሬክተር ጄነራል ሰለሞን በላይ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሳተላይት ባመጠቀች በአራት ቀናት ውስጥ ብቻ ስምንት የአፍሪካ ሀገራት የሳተላይት ምስል ግዢ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ታህሳስ 10 ያመጠቀቻት ሳተላይት የታሰበላትን ቦታ ይዛ ስራዋን በአግባቡ እየሰራች መሆኑ ተገልጿል።
ሳተላይቷ በቀን አስራ አራት ጊዜ በተዘጋጀላት ምህዋር እየዞረች መረጃ የምትሰበስብ ሲሆን በቀን አራት ጊዜ ደግሞ የሰበሰበችውን መረጃ የመቀበል ስራ ይሰራል፡፡
በቀጣይ የኮሙኒኬሽን ሳተላይት ግንባታ እንደሚጀመርና በዘርፉ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
የአፍሪካ የህዋ ኢንዱስትሪ መረጃ
የአፍሪካ የህዋ ኢንዱስትሪ ጅማሮ 21ኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡
እኤአ ከ1998 ጀምሮም የተለያዩ የአህጉሪቱ ሃገራት 41 ሳተላይቶችን ወደ ህዋ አምጥቀዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 38ቱ በ11 ሃገራት የመጠቁ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 3ቱ ደግሞ በሃገራት ዘርፈ ብዙ ትብብር ወደ ህዋ ተልከዋል፡፡
እስካሁን የትኞቹ ሃገራት ምን ያህል ሳተላይቶችን ላኩ?
እስካሁን በአፍሪካ ሀገሮች የተላከ የሳተላይት ቁጥር ብዛት
1.ግብፅ: 9
2. ደቡብ አፍሪካ: 8
3. ናይጄሪያ: 6
4. አልጄሪያ: 6
5. ሞሮኮ: 3
6. በትብብር የተላኩ: 3
7. ኢትዮጵያ: 1
8. ኬንያ: 1
9. ሩዋንዳ: 1
10. ሱዳን: 1
11. አንጎላ: 1
12. ጋና: 1