ኢትዮጵያና ሱዳንን የሚያገናኘው መንገዱ የተዘጋው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ነበር
በመተማ-ጋላባት በኩል ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘው ዋናው መንገድ ከ6ወራት በኋላ ከዛሬ ጀምሮ ክፍት መደረጉን ሱዳን አስታወቀች።
የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል ነቢል አብዱላህ ለአል አይን እንደተናገሩት፤ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የአልገላባት መንገድ ለ7 ወራት ከተዘጋ በኋላ ተከፍቷል።
የሱዳን ጋዳሪፍ ክልል አስተዳዳሪ መሃመድ አብዱልራህማን መሀጁብ በመተማ-ጋላባት በኩል ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘው ዋናው መንገድ በዛሬው እለት በይፋ መከፈቱን አብስረዋል።
አስተዳዳሪው አክለውም አሁን ላይ በሁለቱም ሀገራ ድንበር ላይ ከፍተኛ የሆነ ሰላም እና መረጋጋት መኖሩን ገልጸው፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካካል ያለው ግንኙነትም በጣም ጥሩ ነው ብለዋል።
የመተማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀብቴ አዲሱ ከዚህ ቀደም ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ከሐምሌ 17፣2013ዓ.ም ጀምሮ የመተማ-ጋላባት መንገድ በሱዳን በኩል ተዘግቶ ነበር።
የሱዳን መንግስት መንገዱን የዘጋው አንድ ወታደራዊ አመራር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ተገድሎብኛል ብሎ በማሰቡ መሆኑን አቶ ሀብቴ ተናግረዋል።
ከንቲባው እንዳሉት መንገዱ አለምአቀፍ መስመር ስለሆነ እንዲከፈት በአካባቢው አስተዳደር እና በሀገር ሽማሌዎች ለማስከፈት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
ሱዳን በግዛቷ ውስጥ ለህወሓት ሃይሎች ከለላ በመስጠት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ጥቃት እንዲሰነዝሩ እያደረገች ነው የሚል ክስ በኢትዮጵያ መንግስት ሲቀርብ ነበር።
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ከተጀመራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ወደ ከረረ አለመግባባት ውስጥ ሊገቡ ችለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን ወደ ትግራይ ክልል ባዘመተበት ወቅት የተፈጠረውን ክፍተት እንደመልካም አጋጣሚ በማየት የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቷል በማለት ኢትዮጵያ ትከሳለች። ሱዳን ክሱን ትቀበለውም።