ለ6 ወራት ተዘግቶ የነበረው የኢትዮ-ሱዳን መንገድ ከነገ ጀምሮ ሊከፈት መሆኑ ተገለጸ
መንገዱ የተዘጋው ባለፈው አመት ሐምሌ ወር መሆኑን ከንቲባው አቶ ሀብቴ ገልጸዋል
በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የከረረ አለመግባባት ውስጥ ገብተዋል
በመተማ-ጋላባት በኩል ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘው ዋናው መንገድ ከ6ወራት በኋላ ከነገ ጀምሮ ክፍት እንዲሆን መግባባት ላይ መረደሱ ተገለጸ፡፡
በዛሬው እለት የኢትዮጵያ እና የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች እና የሁለቱ ሀገራት አጎራባቸው አስተዳደሮች ማለትም የምዕራብ ጎንደርና በሱዳን በኩል ደግሞ የጋላባት አካባቢ አስተዳደር ተወካዮች በመተማ ከተማ ተወያይተዋል፡፡
- ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር ጉዳይ ግጭት ውስጥ ቢገቡም የድንበር ላይ ንግዱ አልተቋረጠም-የአካባቢው ባለስልጣን
- ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታ በይፋ ተጀመረ
የመተማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀብቴ አዲሱ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ሐምሌ 17፣2013ዓ.ም የመተማ-ጋላባት መንገድ በሱዳን በኩል ተዘግቶ ነበር፡፡ የሱዳን መንግስት መንገዱን የዘጋው አንድ ወታደራዊ አመራር በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ተገድሎብኛል ብሎ በማሰቡ መሆኑን አቶ ሀብቴ ተናግረዋል፡፡
ከንቲባው እንዳሉት መንገዱ አለምአቀፍ መስመር ስለሆነ እንዲከፈት በአካባቢው አስተዳደር እና በሀገር ሽማሌዎች ለማስከፈት ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
በስብሰባው ላይ መንገዱ ተክፍቶ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲቀጥል መግባባት ላይ መደረሱን የገለጹት አቶ ሀብቴ ከዚህ በተጨማሪም ለሁለቱ ሀገራት አለመግባባት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችም ተነስተዋል ብለዋል፡፡
በሱዳን ግዛት የሚንቀሳቀሱ የህወሓት ኃይሎች መኖራቸውንና ያሉበትን ቦታ ጭምር በመጥቀስ እና ትክክል እንዳልሆነ ለሱዳን ወታደራዊ አመራር እንደተነገራቸው ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ሱዳን በግዛቷ ውስጥ ለህወሓት ሃይሎች ከለላ በመስጠት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ጥቃት እንዲሰነዝሩ እያደረገች ነው የሚል ክስ በኢትዮጵያ መንግስት ሲቀርብ ነበር፡፡
ባለፈው አመት ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ከተጀመራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ወደ ከረረ አለመግባባት ውስጥ ሊገቡ ችለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን ወደ ትግራይ ክልል ባዘመተበት ወቅት የተፈጠረውን ክፍተት እንደመልካም አጋጣሚ በማየት የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቷል በማለት ኢትዮጵያ ትከሳለች፡፡ሱዳን ክሱን ትቀበለውም፡፡
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚያደርጉት ድርድር በተለያየ ጊዜ ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ድንበር እስካሁን መሬት ላይ ያልተሰመረ መሆኑ ሌላኛው ያለመግባባት ምክንያት ሆኖ የቆየ ጉዳይ ነው፤ ይህን ገዳይ ለመፍታት ሀገራቱ የጋራ የድንበር ኮሜቴ በፈረንጆቹ 2020 አቋቁመዋል፡፡