የአዋሽ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ መተሐራ ከተማ በጎርፍ መጥለቅለቋ ተሰማ
ስለ ጎርፍ አደጋው ከመንግሥት የስራ ኃላፊዎች መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም
በአሁኑ ሰዓት ነዋሪዎችን የመታደግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል
የአዋሽ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ መተሐራ ከተማ በጎርፍ መጥለቅለቋ ተሰማ
በኦሮሚ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በመተሐራ ፣ አዲስ ከተማና መርቲ የአዋሽ ወንዝ ከመደበኛ መፍሰሻው ወጥቶ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአል ዐይን ገለጹ፡፡
ነዋሪዎቹ እንዳሉት አሁን ላይ የነፍስ አድንሥራ እየተሰራ ነው፡፡
የሥኳር ፋብሪካው በሚገኝበት መርቲና ከመተሃራ ወደ ሥኳር ፋብሪካው በሚወስደው መንገድ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አዲስ ከተማ ላይ ነው ወንዙ ሰብሮ ጉዳት ያደረሰው፡፡ በጎርፍ አደጋው የደረሰው የአደጋ አይነት እና መጠን በዝርዝር አልታወቀም፡፡
በአሁኑ ሰዓት ጎርፉ አዲስ ከተማን ማጥለቅለቁንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ ከተማ አንቀጸ ሰላም መድኃኒዓለም ገዳም በጎርፉ እንደተጥለቀለቀ የተገለጸ ሲሆን ካህናቱና ዲያቆናቱ የቃልኪዳን ታቦታቱን እና ንዋየ ቅዱሳቱን ይዘው በመተሐራ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እንደሚገኙም ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የገለጹት፡፡
ስለ አደጋው ለመጠየቅ ላይ የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሥራ ሃላፊዎችንና የከተማዋን ባለሥልጣናት ለማግኘት ያረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
በአፋር ክልልም በተመሳሳይ የአዋሽ ወንዝ ሰሞኑን ከመጠን በላይ ሞልቶ ከዋናው መፍሰሻው በመውጣት ጉዳት ማስከተሉ የሚታወስ ሲሆን ዛሬም በክልሉ አሚባራ ወረዳ ጎርፍ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡