በተያዘው ክረምት የወንዙ ሙላት ባስከተለው ጎርፍ በሀገሪቱ የ86 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል
የዓባይ ወንዝ በሱዳን ባለፉት 100 ዓመታት ታይቶ የማያውቅ ከፍታ ላይ ደረሰ
የአባይ ወንዝ ከ 100 ዓመታት ወዲህ ያልደረሰው ያልታሰበ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የሱዳን የመስኖና የውሃ ሀብት ሚኒስቴር ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 21 ቀን 2020 በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡
የወንዙ ከፍታ 17.43 ሜትር የደረሰ ሲሆን እ.ኤ.አ.በ 2019 ተመሳሳይ ወቅት ላይ የነበረው ከፍታ 17.26 ሜትር ነው፡፡ የወንዙን መጠን መለካት ከተጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 1912 ወዲህ የአሁኑን ያህል ከፍታ ባለፉት 100 ዓመታት ተመዝግቦ እንደማያውቅ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በሀገሪቱ ከፍተኛ ጎርፍ በማስከተል ለሰዎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት በመሆን ላይ የሚገኘው የወንዙ ከፍታ ዛሬ 17.44 ሜ. እንደሚደርስም ሚኒስትሩ ያሰር አባስ በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የሱዳን የሀገሩስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው የዘንድሮው የክረምት ወቅት ከተከሰተ ወዲህ የወንዙ ሙላት ባስከተለው ጎርፍ እስካለፈው ማክሰኞ እለት 86 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከ18,000 በላይ ቤቶች ወድመው ተጨማሪ 32,000 ያህል ቤቶች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
የወንዙ ከፍታ ከልክ በላይ እየጨመረ የጎርፍ መጥለቅለቅ በማስከተል ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የመጀመሪያ ዙር ሙሌት ባጠናቀቀችበት ወቅት መሆኑ ግድቡ ባይኖር ወንዙ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ይበልጥ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አመላካች እንደሆነ የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
በቀጣዮቹ ዓመታት የህዳሴው ግድብ የዉሃ ሙሌት ሲጠናቀቅ የጎርፍ አደጋው ሊቆም እንደሚችል የመስኖና የውሃ ሀብት ሚኒስትሩ አባስ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ በቅርቡ በቴክኒክ ቡድኖች (በአገልግሎት ላይ ባለው የጎርፍ ኮሚቴ) ማስጠንቀቂያዎችን ያስተላለፈ መሆኑን ገልፀው በመጪዎቹ ቀናት በሁሉም ወንዙ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች በተለይም በካርቱም እና በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የወንዙ ከፍታ እየጨመረ የሚያስከትለው የጎርፍ አደጋ ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል ብለዋል፡፡
በአባይ ወንዝ እና በገባሮቹ ዳርቻዎች ላይ የሚኖሩ ዜጎች አከባቢቸውንና መንደሮቻቸውን በጋራ በመጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ ሚኒስትሩ ያሰር አባስ ጥሪ አቅርበዋል ሲል የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡