ዩኤኢ የ 300 ቢሊዮን ድርሃም የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ይፋ አድርጋለች
የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ ከ 36 ቢልዮን ዶላር ወደ 82 ቢልዮን ዶላር ለማሳደግ ታቅዷል
ከፍተኛ በጀት የተያዘለት የዩኤኢ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ዓላማ ምንድን ነው?
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዥ ሼህ መሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም በዛሬው እለት የ82 ቢልዮን ዶላር (300 ቢሊዮን ድርሃም ) የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ አስጀምረዋል፡፡ስትራቴጂውን “የትውልዶች የወደፊት ራዕይ እንደማለት ነው" ሲሉም ሼህ መሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም ገልጸዋል፡፡ አክለውም "የዚህ ስትራቴጂ ዋና ዓለማ በሚቀጥሉት ዓመታት 13,500 የኢንዱስትሪ ኩባንያዎች እንዲፈጠሩ ከማገዝ ባለፈ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ጥናትና ምርምር ላይ የሚውለውን ወጪ ከ21 ቢሊዮን ወደ 57 ቢሊዮን ድርሀም ለማሳደግም ያለመ ነው" ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ስትራቴጂው ፣ ዘርፉ ቀደም ሲል ለሀገሪቱ ጥቅል የኢኮኖሚ እድገት እያበረከተ ከነበረው የ36 ቢልዮን ዶላር ፤በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ወደ 82 ቢልዮን ዶላር ለማሳደግ የሚያስችል ነውም ተብሎለታል፡፡
ይህ ስትራቴጂ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ የኢንዱስትሪ መዳረሻዎች አንዷ መሆኗን ለማጠናከር ፣ መንግሥት በፌዴራል ደረጃ የጀመራቸው ጥረቶችና ዕቅዶች አካል ነው፡፡