ዩኤኢ በእስራኤል 10 ቢሊዬን ዶላር ኢንቨስት ልታደርግ ነው
ሃገራቱ ባለፈው ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔዎቻቸውን ፈትተው የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማድረግ መስማማታቸው ይታወሳል
ገንዘቡ “ስትራቴጂክ ናቸው” በተባሉ የተለያዩ የኢነርጂ ልማት እና ሌሎች የልማት መስኮች ፈሰስ የሚደረግ ነው ተብሏል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በእስራኤል 10 ቢሊዬን ዶላር ፈሰስ ለማድረግ የሚያስችላትን የመዋዕለ ንዋይ (ኢንቨስትመንት) ፈንድ ማቋቋሟን አስታወቀች፡፡
ፈንዱ የአቡዳቢው ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር “ገንቢ” የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ የተቋቋመ ነው፡፡
“ስትራቴጂክ ናቸው” በተባሉ የተለያዩ የኢነርጂ ልማት እና ሌሎች የልማት መስኮች ፈሰስ ይደረጋልም ተብሏል፡፡
ይህ መሆኑ የሃገራቱን እና ቀጣናዊ ምጣኔ ሃብታዊ ትብብርን ለማጎልበት እንደሚያግዝ ነው የዩሃገሪቱ የዜና አገልግሎት (ዋም) የዘገበው፡፡
የመንግስትና የግል ተቋማት በፈንዱ የአበርክቶ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
ዋም “ፈንዱበሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ለማጠናከር፤ የኢንቨስትመንት እድሎችንም ለመክፈት በማሰብ በአብራሃም ስምምነት መሰረት የተቋቋመ ነው” ሲል ነው ዋም የዘገበው፡፡
ኒታንያሁ በስልክ በነበራቸው ውይይት ዩኤኢን በቅርቡ የመጎብኘት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡
ይህ በ2 ዓመታት ውስጥ ለ4ኛ ጊዜ ወርሃ መጋቢት መገባደጃ ላይ የሚካሄደው የእስራኤል ጠቅላላ ምርጫ ከመቃረቡ በፊት የሚሆን ነው፡፡
ዩኤኢ እና እስራኤል ዜጎቻቸውን በሙሉ ቀድመው የከተቡ የዓለማችን ሃገራት ናቸው፡፡ ዜጎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ወደ መቆያ ጣቢያዎች እንዲገቡ የማይገደዱበትን ነጻ የንግድ ኮሪደርን ለማመቻቸትም በመነጋር ላይ ናቸው፡፡
ሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔዎቻቸውን ፈትተው የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማድረግ እና በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን “ታሪካዊ” ስምምነት ባለፈው ዓመት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡