ዩኤኢ ዝናብን በሰው ሰራሽ መንገድ ለማዝነብ ከእንግሊዝ ተመራማሪዎች ጋር እየሰራች ነው
ከ5 ዓመታት በፊት ለመሰል 9 የምርምር ፕሮጄክቶች የ15 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ ስለማድረጓም ተነግሯል
ተመራማሪዎቹ በድሮን ታግዘው ለመተግበር ላዘጋጁት የምርምር ስራ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ ማድረጓም ተሰምቷል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩኤኢ) ያላትን አነስተኛ ዓመታዊ የዝናብ መጠን ለማሳደግ ከእንግሊዝ ተመራማሪዎች ጋር እየሰራች ነው ተባለ፡፡
ዩኤኢ በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) በመታገዝና ኤሌክትሪክን ወደ ዳመናዎች በመልቀቅ በአርቴፊሻል መንገድ ዝናብን ለማዝነብ ከሚችሉ የምርምር ተቋማት ጋር በመስራት ላይ መሆኗም ተነግሯል፡፡
ለዚህም ለሬዲንግ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች የምርምር ግኝት ሙከራ 1 ነጥብ 5 ሚሊዬን ዶላር መድባለች ነው የተባለው፡፡
ቴክኖሎጂው ኬሚካሎችን ወደ ዳመና በመልቀቅ ዝናብ እንዲፈጠርና የዝናብ መጠኑ በአማካይ በ30 በመቶ እንዲያድግ ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ከውጭ በሚገቡ የምግብ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት ለማቅለል እንደሚያስችልም ታምኖበታል፡፡
ዩኤኢ 80 በመቶ የምግብ ምርቶችን ከውጭ ነው የምታስገባው፡፡
የተለያዩ የዓለማችን ሃገራት በእንዲህ ዓይነት ሰው ሰራሽ መንገድ ዝናብን ለማዝነብ ሞክረዋል፡፡ ከነዚህ ሃገራት መካከል ቻይና ግንባር ቀደም ነች፡፡
በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሎምፒክ ውድድር የመክፈቻ ስነ ስርዓት ወቅት በነበረው እለታዊ የአየር ሁኔታ ላይ በሰው ሰራሽ መንገድ ተጽዕኖ ለማሳደር ሞክራ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አመታዊ አማካይ የዝናብ መጠኗ ከ100 ሚሊ ሊትር በታች መሆኑን ተከትሎ ዩኤኢ ዓመታዊ የዝናብ መጠኗን ለማሳደግ በመስራት ላይ ነች፡፡ ይህን ጨምሮ በሌሎች የሙከራ ሂደቶችም ላይ ከፍተኛ ገንዘብን ፈሰስ ታደርጋለች፡፡
የሃገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እ.ኤ.አ በ2017 ይህን ጨምሮ ለመሰል 9 የምርምር ፕሮጄክቶች የ15 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍ ማድረጉንም የዝናብ አምጭ ሳይንሳዊ የምርምር ስራዎች ዳይሬክተር አልያ አል ማዙሩይ መናገራቸውን አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡