አረብ ኢምሬትስ በአለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚዋ የከበርቴዎች መዳረሻ መሆኗን ሪፖርት አመላከተ
ሀገሪቱ በ2024 ቀዳሚዋ የሚሊየነሮች መዳረሻ መሆኗ ተገልጿል
በአመቱ ከስድስት ሺህ በላይ ሚሊየነሮች በአቡዳቢ መክተማቸውን ሪፖርቱ አመላቷል
አረብ ኢምሬትስ በ2024 ቀዳሚዋ የሚሊየነሮች መደረሻ መሆኗን ጥናት አመለከተ።
የባለሀብቶችን ከሀገር ሀገር እንቅስቃሴ የሚመዘግበው የሄንሊ ሪፖርት እንደሚያሳየው በአመቱ 6700 ሚሊየነሮች ወደ አረብ ኢምሬትስ አቅንተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ዜጎች እና ብሪታኒያዊያን ሚሊየነሮች ወደ አቡዳቢ በማቅናት ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡
በዱባይ ኑሯቸውን ያደረጉ ሚሊየነሮች ቁጥር ባለፉት አስርተ አመታት በ78 በመቶ ጨምሯል፡፡
የገቢ ግብር የማትሰበስበው አረብ ኢምሬትስ ባለሀብቶች በመኖርያነት እንዲመርጧት ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ቀዳሚው ሲሆን ሀገሪቷ ደረጃውን የጠበቀ አየር መንገድ ባለቤት መሆኗ ደግሞ ተጨማሪ ምክንያት ነው፡፡
ከአረብ ኢምሬትስ ቀጥሎ አሜሪካ በ3800 ሚሊየነሮች ሁለተኛዋ መዳረሻ ስትሆን ሲንጋፖር በ3500 በሶስተኛነት ትከተላለች፡፡
ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ቀጥሎ የአለምን የንግድ ስነስርአት ያዛባው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት በቀደመው ልክ የንግድ እንቅስቃሴን ማድረግ ያልቻሉ ባለሀብቶች የሀብት መጠን እንዲያሽቆለቁል ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ብሉምበርግ በዘገባው ጠቅሷል፡፡
በዚህ የተነሳም በአለም አቀፍ ደረጃ የሚሊየነሮች ቁጥር በመቀነስ ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ ባለፈም የዋጋ ንረት እና የምዕራባዊያን ባንኮች የብድር ወለድ መጨመር ባለጸጎች የተሻለ አሰራር እና አማራጭ ያላቸውን ሀገራት እንዲያማትሩ አድርጓቸዋል ነው የተባለው፡፡
ቻይና በአለም አቀፍ ደረጃ በሚሊየነሮች ፍልሰት ቀዳሚዋ ስለመሆኗ የሚጠቅሰው የብሉምበርግ ዘገባ በአመቱ ቁጥራቸው እስከ 15 ሺህ 200 የሚደርሱ ሚሊየነሮች ሀገሪቷን ለቀው እንደሚወጡ ይጠበቃል ብሏል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የምትገኝው ብሪታንያ በዚህ አመት 9500 ሚሊየነሮቿ ወደ ሌሎች ሀገራት የፈለሱባት ሲሆን እስከ አመቱ መጨረሻ ሀገሪቷን ጥለው ለመሰደድ ያሰቡ ባለጸጎች ቁጥር በ2023 ከነበረው እጥፍ መሆኑ ተመላክቷል፡፡