የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በዪኤኢ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት አወገዘ
በዩኤኢ ጉዳይ የሁቲ ታጣቂዎች የሚያወግዘው መግለጫ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁም ተነግሯል
ባለፈው ሰኞ በዩኤኢ ሲቪል ተቋማት ላይ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት ከፍተኛ ውግዘት እንዳስከተለ ነው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በየመን የሚንቀሳቀሱት የሁሲ አማጽያን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ላይ ያደረሱትን የሽብር ጥቃት አወገዘ።
ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ “የሁሲ አማጽያን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ርዕሰ መዲና አቡ ዳቢ ውስጥ፤ በሲቪል ተቋማት ላይ ያደረሱት አረመኔያዊ የሽብር ጥቃት የምክር ቤቱ አባላት አጥብቀው እንደሚያወግዙ” አስታውቋል።
ከጥር 1 ጀምሮ የምክር ቤቱ ቋሚ አባል በሆነችው የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጠያቂነት በዝግ ስብሰባ የመከረው ምክር ቤቱ በዩኤኢ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ጥቃት የፈፀሙት የሁሲ ታጣቂዎች መሆናቸውን የሚያመለክተው መግለጫን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ፤ በቀጣይ ሊፈጸሙ የሚችሉትን መሰል ጥቃቶችን ለመቋቋምም ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ድጋፍ እንደሚሰጥም አረጋግጧል።
ባለፈው ሰኞ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሲቪል ተቋማት ላይ የተፈጸመው የሽብር ጥቃት ከፍተኛ ውግዘት እንዳስከተለ ይታወቃል።
አፍሪካ ህብረት በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አቡዳቢ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት ማውገዙ የሚታወስ ነው። ለኤሜሬቶች ህዝብና መንግስት እንዲሁም ለተጎጂ ቤተሰቦችም ጭምር መጽናናትን ተመኝቷል።
ኢትዮጵያም ንጹሃንን ኢላማ አድርጓል የተባለውን የሽብር ድርጊት በማውገዝ ለዩኤኢ ያላትን አጋርነት ማሳየቷ የሚታወስ ነው።
ጎረቤት ሃገር ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኮትዲቯር፣ ጋና፣ ኒጀር እና ደቡብ አፍሪካም ድርጊቱን በማውገዝ አጋርነታቸውን ገልጸዋል።
ሳዑዲ አረቢያን፣ ግብጽን፣ ኩዌትን የመሳሰሉ የአረብ ሃገራትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ድርጊቱን በማውገዝ ከዩኤኢ ህዝብና መንግስት ጎን መሆናቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው፡፡
የአቡዳቢ ፖሊስ አድኖክ (ADNOC) በተሰኘ ግዙፈ የነዳጅ ታንከሮች አቅራቢያ በሚገኘው Musaffah ICAD-3 አካባቢ በተፈጸመው ጥቃት 3 ሰዎች መሞታቸውን እና 6 ሰዎች መቁሰላቸውን ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ አይዘነጋም።
“በአደጋው የአንድ ፓኪስታን እና የሁለት ህንድ ዜጎች ህይወት ሲያልፍ ሌሎች 6 ሰዎች ደግሞ ቀላል እና መካከለኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል”ም ነበር ያለው መግለጫው።