የአፍሪካ ህብረት በዩኤኢ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት አወገዘ
ጥቃቱን ያወገዙት የህብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽን ሊቀመንበር ለኤመራት ህዝብና መንግስት መጽናናትን ተመኝተዋል
አፍሪካም የእንዲህ ዐይነት የሽብር ጥቃቶች ተቀዳሚ ሰለባ ነች ያለው ህብረቱ የጸረ ሽብር ትግሎች እንዲጠናከሩ ጥሪ አቅርቧል
የአፍሪካ ህብረት ባሳለፍነው ሰኞ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አቡዳቢ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት አወገዘ፡፡
በጥቃቱ ማዘናቸውን የገለጹት የህብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት “አረመኔያዊ” ያሉትን ድርጊቱን በጽኑ አውግዘዋል፡፡
ለኤመራት ህዝብና መንግስት ለተጎጂ ቤተሰቦች ጭምር መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
አፍሪካም የእንዲህ ዐይነት የሽብር ጥቃቶች ተቀዳሚ ሰለባ ነች ያሉት ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ዓለም አቀፉ የጸረ ሽብር ትግል የበለጠ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያም ንጹሃንን ኢላማ አድርጓል የተባለውን የሽብር ድርጊት በማውገዝ ለዩኤኢ ያላትን አጋርነት ማሳየቷ የሚታወስ ነው፡፡
ጎረቤት ሃገር ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኮትዲቯር፣ ጋና፣ ኒጀር እና ደቡብ አፍሪካም ድርጊቱን በማውገዝ አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያን፣ ግብጽን፣ ኩዌትን የመሳሰሉ የአረብ ሃገራትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ድርጊቱን በማውገዝ ከዩኤኢ ህዝብና መንግስት ጎን መሆናቸውን ማሳወቃቸውም ይታወሳል፡፡
በየመን የሚንቀሳቀሱት የሁሲ አማጽያን በፈጸሙት በዚህ ጥቃት ሲቪል ዜጎችን መግደላቸውና የሲቪሊያን መገልገያ የነበሩ መሰረተ ልማቶችን ማውደማቸው ይታወቃል፡፡
ንጹሃንን ዒላማ ያደረገውን ይህን ጥቃት “ሰይጣናዊ” ስትል ያወገዘችው ዩኤኢ ጥቃቱ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚያሻው በመጠቆም ምላሽ የመስጠት መብቷን እንደምትጠቀም ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡