አሜሪካ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችው አቋም የግለሰቦች ወይስ የሀገሪቱ አቋም?
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል
“የዓለም ጤና ድርጅት በአማራ እና አፋር ክልሎች በህወሃት በወደሙ ጤና ተቋማት ላይ ምንም አለማለቱ ገርሞናል”-አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ስለ ኢትዮጵያ-አሜሪካ ግንኙነት፣ ለገና በዓል ይመጣሉ ስለተባሉት ዲያስፖራዎች፣ ስለ ጄፍሪ ፌልትማን የካይሮ እና አቡዳቢ ጉብኝት፣ ህወሃት በጤና ተቋማት ላይ ስላደረሰው ጉዳት እና ጉዳዩ ስለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ዝምታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ኢትዮጵያ ይጠላሉ ይባላል። አሜሪካ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችው አቋም የግለሰቦች ነው ወይስ የመንግስት አቋም ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቅ አምባሳደር ዲና ተከታዩን ብለዋል።
“የአሜሪካ አስተዳድር ዳይቨርስ ነው፣ አማካሪዎች፣ ሴናተሮች፣ ፓርቲዎች እና ሌሎችም አሉ፤ እዚህ ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጻረሩ አሉ፤ እነዚህ ለጥቅማቸው ሲሉ ነው የሚሰሩት በሎቢስት እና በአክቲቪስት የተገዙ ናቸው። ጥቅም እስካገኙ ድረስ የኢትዮጵያን ጥቅም ይጻረራሉ። ነጻ የውጭ ዲፕሎማሲ የሚከተሉ ሀገራት አይመቿቸውም፤ ይሁንና በአሁኑ አስተዳድር ውስጥ ከህወሃት ጋር ለጥቅማቸው የሚሰሩ አሉ፤ ስለዚህ ጉዳዩን ከዚህ አንጻር ነው የሚታየው” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች በከፈተው ጥቃት 8 ሚሊዮን ዜጎች ተፈናቅለው፣ በርካታ የጤና ተቋማት መውደማቸውን የዓለም ጤና ድርጅት እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንዳልሰሙ መሆናቸው ያስተዛዝባል ብለዋል።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ግብጽ፣ዩኤኢ እና ቱርክ ተጉዘው በኢትዮጵያ ጉዳይ መምከራቸው ይታወሳል።
መልዕክተኛው ወደ ሶስቱ አገራት ጋር የመከሩባቸው አጀንዳዎችን ኢትዮጵያ ታውቃለች? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ጄፍሪ ፊልትማን ከሶስቱ አገራት ጋር በምን ጉዳይ እንደመከሩ መረጃ የለንም ብለዋል።
አዲስ አበባ ያሉ አንዳንድ ኢምባሲዎች ዜጎቻቸው አሁንም ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ በማሳሰብ ላይ ናቸው፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እነዚህ አካላት ጠርቶ ማብራሪያ እንዲሰጠው ለምን አይጠይቅም ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄም “ሁሉም የዲፕሎማሲ ስራ ለሚዲያ ክፍት ስለማይሆን እንጂ ብዙ ስራዎችን እየሰራን ነው” ብለዋል።