አሜሪካ “የትግራይ ኃይሎች” በአማራና አፋር ግፍ መፈጸማቸውን አስታወቀች
የፈፀሙት የሰብአዊ መብቶች ረገጣና መሰረተ ልማቶችን ማውደማቸው እንዳሳሰባት አስታውቃለች
ወንጀሎቹን የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድ እንዲፈጠር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጠይቋል
ዋሸንግተን “የትግራይ ኃይሎች” በአማራ እና አፋር ክልሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ፣ ግፍ እና የንጹሃንን መሰረተ ልማቶችን ማውደማቸው እንዳሳሰባት አስታወቀች።
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መኖሩን፣ ግፍና መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን ባልተረጋገጡ መረጃዎች መረዳቱንም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።
በዚህም መሰረት አሜሪካ ጉዳዩ እንዳሳሰባት የገለጸች ሲሆን ሁሉም የታጠቁ ወገኖች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እንዲያቆሙ ጠይቃለች።
ባለሥልጣናት እነዚህ የመብት ጥሰቶች እንዲመረመሩ ማድረግ እንዳለባቸውም ዋሸንግተን ጥሪ ያቀረበች ሲሆን፤ ይህም ሁሉንም አሳታፊና ግልጽ እንዲሆን ጠይቃለች።
ነዚህን ወንጀሎች የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት መንገድም እንዲፈጠር ነው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያስታወቀው፡፡
አሜሪካ፤ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም መፍትሄ ዲፕሎማሲ መሆኑን እንደምታምን እና ይህም ግጭቱን ለማስቆም ብቸኛ አማራጭ እንደሆነም ገልጻለች። ለዚህ ጥረትም ዋሸንግተን ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ድርድር እንዲደረግ በተደጋጋሚ ስትጠይቅ የነበረችው አሜሪካ ይህንን አሁንም ደግማ ጠይቃለች።
ያልተገደበ የሰብዓዊ አቅርቦት እና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት መጀመር እንዳለበትም አሜሪካ ገልጻለች።