ቃል አቀባዩ አሜሪካ እርምጃ ከህዳሴው ግድብ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ተናግረዋል
የአሜሪካ የጉዞ ቪዛ ክልከላ ጉዳይ ከህዳሴው ግድብ ሊገናኝ እንደሚችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።
“ክልከላው ለአሜሪካም አይጠቅምም” ያሉት ቃል አቀባዩ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት የለውም ሲሉ ዛሬ የሚኒስቴሩን ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው “ለዚህ የሚያበቃ ምንም ምክንያት የለም” ያሉ ሲሆን “የአሜሪካ ፍላጐት በእኛ (በኢትዮጵያ) ፍላጎት ኪሳራ ላይ መሆን የለበትም” ሲሉ ተናግረዋል።
አምባሳደር ዲና ሲያሟግተን የነበረው የሰብዓዊ አቅርቦት ጉዳይ ተፈቷል ብለዋል፡፡ አሉ የተባሉ ጥሰቶች እየተጣሩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑንም ነው የገለጹት።
“ይሄ ለምን ይካዳል፤ መረጃ ስላልደረሳቸው ስላላወቁም አይደለም” ሲሉ የሚያጠይቁት አምባሳደር ዲና አውቆ የሚደረግ “ጥቅም የመፈለግ፣ በቁጥጥር ስር የማድረግ እና በተጽዕኖ ስር የማሳደር ዝንባሌ” እንደሆነም ያስቀምጣሉ።
ኢትዮጵያ ከአንዳንድ ሃገራት ጋር ያላት የኢንቨስትመንትና ሌላም ግንኙነት አሜሪካን ሊያስደስት እንደማይችልም ነው የሚገልጹት፡፡
ግንኙነቱ እንዲበላሽ አንፈልግም በሚል የተናገሩት ቃል አቀባዩ ነገር ግን “ሉዓላዊነት የሚባል ቀይ መስመር አለ” ሲሉ አክለዋል፤ መስመሩ ሊጣስ እንደማይገባ እና እንዲጣስ የሚፈቅድ አካል እንደሌለም በመጠቆም፡፡
“እንዲህ ዓይነት ታሪክ የለንም”ም ነው ያሉት አምባሳደር ዲና።
ጉዳዩን “በይደር ማየቱ ጠቃሚ ነው” ያሉም ሲሆን አሜሪካ በኢትዮጵያ ምን ያህል ኢንቨስት ታደርጋለች የሚለውን ማየቱ እንደሚጠቅም ጠቁመዋል።
ቃል አቀባዩ ማዕቀቡ ከህዳሴው ግድቡ ጋር ሊገናኝ የሚችልባቸው መንገዶች ሊኖሩ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
አሜሪካ ከአሁን ቀደም ግድቡን በተመለከተ ጫን ያለ የተደራደሩ አቋም እንደነበራት ይታወሳል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በዋሽንግተን ሲካሄድ ከነበረው የድርድር ሂደት አፈንግጣ መውጣቷ አይዘነጋም፡፡
በቅርቡ የፕሬዝዳንት ባይደን የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕተኛ ሆነው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ጄፍሪ ፌልትማን ስለ ግድቡ ድርድር ጉዳይም አንስተው ከባለስልጣናቱ ጋር መወያየታቸውንና ኢትዮጵያም አቋሟን በግልጽ እንዳሳወቀቻቸው አምባሰደር ዲና ገልጸዋል፡፡