የዓለም ባንክ በማሊ የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጡን አስታወቀ
ባንኩ በማሊ እየተሰሩ ላሉ የልማት ስራዎች የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፍ በጊዜያዊነት አቋርጧል
በምዕርብ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ በአገሪቱ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሟል
የዓለም ባንክ በማሊ በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ምክንያት ለሀገሪቱ የሚያደርገውን የገንዘብ ድጋፎች ማቋረጡን አስታወቀ።
የዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፉን መቋረጡን የገለጸው በምዕርብ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ በአገሪቱ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት መደረጉን ተከትሎ እንደሆነም አስታውቋል።
የባንኩ የባማኮ ቢሮ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ መቀመጫውን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የዓለም ባንክ በማሊ እየተሰሩ ላሉ የልማት ስራዎች የሚያደርገውን ገንዘብ ድጋፍ በጊዜያዊነት አቋርጧል።
የዓለም ባንክ በማሊ ያለውን ሁኔታም ባንኩ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንም ቃል አቀባዩ አክለው አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ህብረትም ከዚህ በፊት በማሊ ላይ ጥሎት የነበረውን ከአባልነት የማገድ ውሳኔ ፣ በማሊ በህዝብ ምርጫ የተመሰረተ መንግስት ስልጣን እስኪይዝ ድረስ ማራዘሙ ይታወሳል።
15 አባል አገራት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) በማሊ በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ምክንያት አስተላልፎት የነበረውን ከአባልነት የማገድ ውሳኔ በድጋሚ ማራዘሙ አይዘነጋም።
በምዕርብ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ በአገሪቱ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሟል።
የ38 ዓመቱ ኮሎኔል ጎይታ ከዘጠኝ ወር በፊት በወቅቱ የማሊ ፕሬዝደንት አቡበከር ኬታ ላይ በፈጸሙት መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ቢቆጣጠሩም ከምዕራባዊያን እና አሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲሰጡ ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው በኋላ እራሳቸውን ምክትል ፕሬዝዳንት በማድረግ አዲስ ፕሬዘዳንት እና ጠቅላላ ሚንስትር እንዲሰየም አድርገው ቆይተዋል።
ይሁንና ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሬዝዳንቱን እና ጠቅላይ ሚንስትሩን በማሰር ራሳቸውን የማሊ የሽግግር ጊዜ ፕሬዘዳንት አድርገው ሾመዋል።
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ባሳለፍነው ሳምንት በጋና አክራ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ማሊን ከክፍለ አህጉር አባልነት አግዷል።
የኢኮዋስ ውሳኔን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረትም ማሊን ከአባልነት እንድትታገድ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለማሊ የገንዘብ እርዳታ እንዳያደርጉ አሳስቦ ነበር።