ወታደራዊ ያልሆነ አስተዳደር እንዲመሰረት የሚጠይቅ ሰልፍ በሱዳን ተካሂዷል
የሱዳን ጦር የሀገሪቱ እንጅ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱን የሚመሩት የአብዱል ፋታህ አል ቡርሃን መሆን እንደሌለበት የካርቱም ሰልፈኞች ተናግረዋል፡፡
ወታደራዊ ያልሆነ መንግስት እንዲመሰረት የሚጠይቅ ሰልፍ በሱዳን መዲና ካርቱም ትናንትና የተካሄደ ሲሆን ሰልፈኞቹ የሀገሪቱን ጦር እና ሌሎችንም የተመለከቱ መልዕክቶች አስተላልፈዋል፡፡ የሱዳንን ሰንደቅ ዓለማ በማውለብለብ ሰልፍ ያደረጉ ዜጎች ጦሩ የሱዳን እንጅ የአል ቡርሃን አይደለም ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሰልፉ ላይ 20 ሺ የሚገመት ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ወታደራዊ ያልሆነ መንግስት (ሲቪል) እንዲመሰረት መጠየቁን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን የሱዳን የጸጥታ ኃይሎችም በሰልፈኞቹ ለይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል ተብሏል፡፡
የሰልፉ ተሳታፊዎች ከዋና ከተማዋ ካርቱም ውጭ ማለትም ከአትባራ እና ማዳኒ መምጣታቸው ተገልጿል፡፡ ባለፈው ሳምንት በሱዳን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ባለስልጣናት ይህንን ያደረጉ አካላት የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ኦማር ሃሰን አልበሽር ታማኞች ናቸው ብለው ነበር፡፡
በርካታ ዜጎች ከማዳኒ ከተማ የተነሳው ባቡር ካርቱም ሲደርስ ደስታቸውን የገለጹ ሰሆን ወደ ባቡሩ የመጨረሻ ደረጃ እየወጡ ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ ነበር፡፡ በዚህም ወታደሩ የሀገር እንጅ የግለሰብ አይደለም የሚል መልዕክት የያዙ ሰልፈኞች እንደነበሩ ተገልጿል፡፡
ከሰልፈኞቹ መካከል የ 22 ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪው ኢማም ሳሊህ “እኛ እዚህ የመጣነው የሲቪል አስተዳደር እንዲመሰረት ለመጠየቅ ነው፤ ወታደሩ አብዮታችንን እንዲቆጣጠረው አንፈልግም” ብሏል፡፡ አሁን በሱዳን ያሉ የሲቪል ባለስልጣናት ለሰልፈኞቹ ሰላምታ መስተታቸው የተገለጸ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎች ግን አስለቃሽ ጭስ እንደተኮሱባቸው ተገልጿል፡፡ ይህ ደግሞ በጦሩ እና በሲቪል አመራሮች መካከል ያለውን መቃቃር እንዲሚያሳይ ነው የተነገረው፡፡ ከመፈንቅለ መንግስቱ መኩራ በኋላ ሲቪል አመራሮቹ ወታደሩን ፤ወታደሩ ደግሞ ሲቪል አመራሮችን እየወቀሱ ናቸው፡፡