የሱዳን ጦር መሪ ወታደራዊ ሪፎርሞችን ለማድረግ ቃል ገቡ
ቡርሃን የሚመሩት ጦር ከሰሞኑ የተፈጸመውንና “በአልበሽር ታማኞች” የተመራ ነው ያለውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዳከሸፈ ማስታወቁ የሚታወስ ነው
ሌ/ጄ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ጦሩን እንደገና እናደራጀዋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል
የሱዳን ወታደራዊ መዋቅር ሪፎርም እንደሚያደረጉ የሀገሪቱ ሉዓላዊ ምክር ቤት ኃላፊ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ገለጹ፡፡
ጀነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ይህንን ያሉት ከቀናት በፊት በሀገሪቱ የተደረገው ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስትን ተከትሎ ነው፡፡
"ወታደራዊ ኃይሉን እንደገና እናደራጀዋለን….በወታደር ቤት ማንኛውም ዓይነት ለፓርቲ ያዘነበለ ተግባር ማከናወን ክልክል ነው"ም ብለዋል ጀነራሉ፡፡
“ሱዳንን ለማሸነፍ የሚችል ኃይል የለም”- አል ቡርሃን
ቡርሃን እንደፈረንጆቹ በ2023 የሚካሄደውን ምርጫ ለማከናውን ወታደራዊ ኃይሉ ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ከምርጫ በኋላ ወታደራዊ ኃይሉ በፖለቲካ ያለውን ሚና አብቅቶ፤ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ወደ ሚያስከብርበት ዋናው ስራው የሚያተኩር ይሆናልም ብለዋል፡፡
ሱዳን የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልበሽር ከስልጣን መወገድን ተከትሎ፤ እንደፈረንጆቹ ከነሃሴ 2019 ጀምሮ በሲቪል እና ወታደራዊ ሃይሎች ጥምረት በተቋቋመው የሽግግር መንግስት በመመራት ላይ ያለች ሀገር ናት፡፡
ሀገሪቱ በዚህ ሳምንት ያስተናገደችው ያልተሳካ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ፤ በቀድሞው ፕሬዝዳንት አልበሽር ታማኝ ወታደራዊ መኮንኖች የተሸረበ ሴራ እንደሆነም እየተነገረ ይገኛል፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን ከመሩትና በቁጥጥር ስር ከዋሉት ወታደራዊ መኮንኖች 11 የሚሆኑት የአልበሽር ሰዎች ናቸውም ነው የተባለው፡፡
የሱዳን መፈንቅለ መንግስት ሙከራን ተከትሎ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች እየተካሰሱ ነው
እንደ ጀነራል አል-ቡርሃን ሁላ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክም ወታደራዊ ኃይሉ ሪፎርም እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጂ በሱዳን እየታየ ባለው የፖለቲካ ቡድንተኝነት እና ኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ወደ ሲቪል አገዛዝ የሚደረግ ሽግግር እንዳይኮለሽ በርካቶች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንትና የፓርላማ ኃላፊው ጀነራል ሞሃመድ ሃምዳን ደገሎ ለመፈንቅለ መንግሰቱ ፖለቲከኞችን ተጠያቂ አድርጓል፡፡
"ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች በስተጀርባ ፖለቲከኞች አሉ ምክንያቱም ተራውን ዜጋ ችላ በማለት ስልጣን ላይ እንዴት መቆየት እንችላለን የሚል ኃሳብ ስላላቸው ነው" ብሏል ደገሎ፡፡