የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ከ40 ዓመት በኋላ ለጉብኝት ሱዳን ገብተዋል
ፕሬዝዳንቱ በሀገሪቱ ወታደራዊ አመራሮችና በሲቪሉ አስተዳድር መካከል የፖለቲካ መከዳዳት ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል
ሱዳን በለውጥ ላይ መሆኗ ቢደነቅም የፖለቲካ አለመተማመን ችግር እንዳለባት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል
የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ዴቪድ ማልፓስ ሱዳንን በመጎብኘት ላይ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ ትናንት ምሽት ካርቱም የደረሱ ሲሆን የዴቪድ ማልፓሳ ጉብኝት የባንኩ ከፍተኛ ሃላፊዎች ካርቱምን ሲጎበኙ ከ40 ዓመት በኋላ ነው ተብሏል።
ሱዳን በለውጥ ላይ መሆኗን ያደነቁት ፕሬዝዳንቱ በአገሪቱ ወታደራዊ አመራሮች እና በሲቪሉ አስተዳድር መካከል የፖለቲካ መከዳዳት ሊኖር እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዝግቧል።
ሱዳን የሽብር ድኖችን ትደግፋለች በሚል በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቀብ ከአንድ ዓመት በፊት መነሳቱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የገንዝብ ተቋማት ለሱዳን ብድሮችን ከመሰረዝ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማግኘት ላይ እንደምትገኝም ተገልጿል።
ለአብነትም በሱዳን አዲስ የፖለቲካ ስርዓት መጀመሩን ተከትሎ እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር የብድር እፎይታ እንድታገኝ የተደረገላት ሲሆን ድጋፉ በዓለማችን ባለፉት ሁለት ዓመታት ድጋፍ ከተደረገላቸው አገራት መካከል ቀዳሚዋ አገር አድርጓታል።
ይሁንና አሁንም የሱዳን ኢኮኖሚ በኮሮና ቫይረስ፤በጎርፍ እና በሌሎች ችግሮች እየተፈተነ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት እና የሲቪል አስተዳድሩ ለሱዳን አንድነት እና የተሻለች አገር ለመገንባት በጋራ እንዲሰሩም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሱዳን ከሁለት ሳምንት በፊት ተሞከረ የተባለ መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን መነሻ አድርገው ባሰሙት ንግግርም የሱዳን ወታደራዊ እና የሲቪል አስተዳድር አመራሮች በመካከላቸው የፖለተካ መተማመንን ሊያጎለብቱ ይገባልም ብለዋል።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ከሁለት ዓመት በፊት በህዝብ ግፊት ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት እና የሲቪል አስተዳድሩ በምርጫ የተመረጠ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ እየተፈራረቁ አገሪቱን እንዲመሩ ተስማምተው ነበር።
በቅድሚያም የሱዳን ወታደራዊ ከንፉን የሚመሩት ሌተናንት ጀነራል አልቡርሃን አልሲሲ ሱዳንን መምራት የጀመሩ ሲሆን የፊታችን ህዳር ስልጣናቸውን በዶክተር አብደላ ሀምዶክ ለሚመራው የሲቪል አስተዳድር እንደሚያስረክቡ ይጠበቃል።
ይሁንና ወታደራዊ ክንፉ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር ላያስረክብ ይችላል የሚሉ ስጋቶች በመነሳት ላይ ናቸው።