እስራኤል የኢራንን ጥቃት ለመከላከል የተጠቀመቻቸው 3 የሚሳይል መከላከያ ስርአቶች
የእስራኤል እና የአሜሪካ የሚሳይል መከላከያ ስርአቶች ጥምረት በመፍጠር ይህን ያልተጠበቀ ጥቃት ተከላክለዋል
ከሁለት ቀናት በፊት ኢራን ካስወነጨፈቻቸው 300 ሚሳይሎች እና ድሮኖችን ውስጥ አብዛኞቹ መክሸፋቸውን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል
እስራኤል የኢራንን ጥቃት ለመከላከል የተጠቀመቻቸው 3 የሚሳይል መከላከያ ስርአቶች
ከሁለት ቀናት በፊት ኢራን ለአምስት ሰአታት 300 ሚሳይሎች እና ድሮኖችን ወደ እስራኤል ብታስወነጭፍም አብዛኞቹ መክሸፋቸውን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የእስራኤል እና የአሜሪካ የሚሳይል መከላከያ ስርአቶች ጥምረት በመፍጠር ይህን ያልተጠበቀ ጥቃት ተከላክለዋል።
- አሜሪካ “እስራኤል በኢራን ላይ በምትወስደው የአጻፋ እርምጃ እጄን አላስገባም” አለች
- ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ የበረራ መስተጓጎል አጋጠመ
አሜሪካ ቢሊየን ዶላሮች በማፍስስ ውስብስብ እና በርካታ እርከን (መልቲሌየርድ) የመከላከያ ስርአት እንዲቋቋም ያደረገች ሲሆን ከጥቅምቱ የሀማስ ጥቃት በኋላ ደግሞ ለእስራኤል ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ ለመስጠት ሀሳብ አቅርባለች።
"አክሽፈነዋል። አብረን ሆነን እናሸንፋለን።" ሲሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጥቃቱ በኋላ ተናግረዋል።
አይረን ዶም
በእስራኤል አየር መከላከያ ውስጥ ወሳኙ 'አይረን ዶም' የተሰራው በእስራኤሉ ራፋኤል አድቫንስድ ዲፌንስ ሲስተምስ እና በእስራኤል ኤሮስፔስ ኢንዱስትሪ ነው። የአይረን ዶም ሚሳይል መከላከያ ስርአት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በ2011 ሲሆን አላማውም በሀማስ እና በእስላሚክ ጅሀድ የሚወነጨፉ የአጭር ርቀት ሚሳይሎችን ማክሸፍ ነበር።
ይህ ስርአት ከራዳራ በሚያገኘው መረጃ መሰረት እየመጣ ያለው ሚሳይል ህዝብ በበዛበት ቦታ ወይም ወሳኝ መሰረተ ልማት ባለበት ቦታ ያርፋል ብሎ ግምት ከወሰደ ተኩሶ ያከሸፋል።
የእስራኤል ባለስልጣናት እና የመከላከያ ኩባንያዎች እንደሚሉት ከሆነ የአይረን ዶም የስኬት ምጥነቱ 90 በመቶ ነው።
ዴቪድስ ስሊንግ
በእስራኤል የአየር መከላከያ ኔትዎርክ ውስጥ በሁለተኛ እርከን ላይ እና ባለስቲክ ሚሳይሎች እና ክሩዝ ሚሳይሎችን እንዲሁም ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ለማክሸፍ የተሰራ ነው።
በራፋኤል አድቫንስድ ዲፌንስ ሲስተም እና በግዙፉ የአሜሪካ መከላከያ ኮንትራክተር ራይቲዮን የተሰራው ዴቪድ ስሊንግ ሮኬቶች እና ሚሳይሎችን ከ25 እስከ 186 ማይል ድረስ ባለው ርቀት ውስጥ ለማክሸፍ ጥቅም ላይ ይውላል።
አሮው
አሮው 2 እና እሮው 3 ስርአቶች ከመሬት ከባቢ አየር ውጭ የሚወነጨፉ ሚሳይሎችን ለማክሸፍ የተሰሩ ናቸው። በ2017 የተጠናቀቀው አሮው-3፣ ባለፈው አመት በኢራን የሚደገፉት የሀውቲ ታጣቂዎች ወደ ኢላት ያስወነጨፉትን ሚሳይል በማክሸፍ ተሞክሯል።
አሮው-3 የተሰራው በእስራኤል እና አሜሪካ ጥምረት ነው።
ጥቃቶቹ የሚሰነዘሩት ከኢራን፣ ከኢራቅ፣ ከየመን እና ከሶሪያ ሲሆን እንግሊዝን እና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ ሀገራትን የያዘው በአሜሪካ የሚመራው ጥምረት ለእስራኤል ወሳኝ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል።
የአሜሪካ እና የእግሊዝ ጦር ኢራን ያስወነጨፈቻቸውን ሚሳይሎች በማክሸፍ መሳተፋቸውን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳይል ጥቃት የሰነዘረችው በሶሪያ ደማስቆ የሚኘው ኢምባሲዋ ጥቃት አደረሰበት በኋላ ነው።
ለኢምባሲዋ ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገችው ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት እንደምታደርስ ስትዝት ነበር።