ኢትዮጵያ በዓለም የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2ኛውን የወርቅ ሜደሊያ አገኘች
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ እስካሁን 2 የወርቅ፣ 4 የብር እና 2 የነሃስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች
በዓለም የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ከዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
በ18ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኬኒያ አስተናጋጅነት በናይሮቢ መካሄድ ከጀመረ በዛሬ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
በኬንያ ናይሮቢ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ሴቶች ውድድር አትሌት አያል ዳኛቸው በ2:02.96 በሆነ ሰዓት 1ኛ በመውጣት ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ለኢትዮጵያ አስመዝግባለች።
ኢትዮጵያ መጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በወንዶች 3000 ሜትር ውድድር በአትሌት ታደሰ ወርቁ አማካኝነት ማግኘቷ የሚታወስ ሲሆን፤ በርቀቱ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አሊ አብዱልመና 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በ3000 ሜትር የውርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ታደሰ ወርቁ፤ በወንዶች 5000 ሜትር ፍፃሜ ውድድር ላይ ተሳትፎ ርቀቱን በ13:20.65 በሆነ ሰዓት 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ማስገኘቱ ይታወሳል።
በሌላ በኩል በ1500 ሜትር ወንዶች ውድድር የተሳተፋት አትሌት ወገኔ አዲሱ በ3:37.86 በሆነ ሰዓት 2ኛ አትሌት መልኬነህ አዘዘ በ3:40.22 በሆነ ሰዓት 3ኛ በመውጣት የብር እና የነሀስ ሜዳልያዎችን አስገኝተዋል።
በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ውድድር ላይም አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ በ9:35.22 በሆነ ሰዓት 2ኛ በመውጣት የብር ሜዳልያ አስገኝታለች።
በሴቶች 3000 ሜትር ውድድር ኢትዮጵያን በብቸኝነት የወከለችው አትሌት መልክናት ውዱ በ9:00.12 በሆነ የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባ ሶስተኛ በመውጣት የነሀስ ሜዳልያ አስገኝታለች።
በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ እስካሁን 2 የወርቅ፣ 4 የብር እና 2 የነሃስ በድምሩ 8 ሜዳሊያዎችን ማሰባሰብ የቻለች ሲሆን፤ በሜዳሊያ ሰንተረዥ ኢትዮጵያ ከዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ኬንያ 5 የወርቅ፣ 1 የብር እና 3 የነሃስ በድምሩ 1 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ 1ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ ፊንላንድ 3 የወርቅ እና 1 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በ18ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች (ወጣቶች) አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ከ400 ሜትር ጀምሮ በ8 የውድድር አይነቶች እንደምትሳተፍ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ፤ ከአጭር ርቀት ጀምሮ ወጣቶች በሚሳተፉባቸው የረጅም ርቀቶች፣ በ3000ሜ.መሰናክልና በእርምጃ ውድድሮች የምትካፈል ሲሆን በ10 ወንድ፣ በ15 ሴት እና በአጠቃይ በ25 አትሌቶች ተወክላለች።