የመንግስት አግልግሎትን፣ መሰረተ ልማቶችንና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ወደ ስራ ማስገባት የእቅዱ አካል ነው
የገንዘብ ሚኒስቴር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በባለድርሻ አካላት የቀረበላቸውን ምክረ ሀሳብ ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ ማገገሚያ እቅድ ይፋ አድርገዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ ማገገሚያ እቅዱ ላይ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመቐለ ከተማ ከተወያዩ በኋላ ነው እቅዱን ይፋ ያደረጉት።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የማገገሚያ እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በፍጥነት መጀመር በቶሎ ለማገገም እና ለረጅም ጊዜ በሰብዓዊ ድጋፎች ላይ ጥገኛ ላለመሆን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሁሉም መስሪያ ቤቶች የአስቸኳይ ጊዜ ማገገሚያ እቅዱ ወደ ስራ እንዲገባ ሙሉ ኃላፊነቱን ወስደው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ ያስሚን ዎሃበርቢ በበኩላቸው፤ የአስቸኳይ ጊዜ ማገገሚያ እቅዱ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ በክልሉ የደረሰውን ጉዳት ለማከም እንዲሁም ለመልሶ ማቋቋም እና ማገገም ቅደሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትን በመለየት የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
በእቅዱ ዝግጅት ላይም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሙያዎችን ጨምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተወካዮች እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ መሳተፋቸውን አስታውቀዋል።
እቅዱ በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ማህበራዊ አንድነትን፣ መተማመን እና መረጋጋትን መልሶ በመገንባት የነዋሪዎችን ሰላምና ተጠቃሚነት ማረጋገጥን አላማው ያደረገ መሆኑንም ነው የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው።
ከዚህ ባለፈም በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመንግስት አግልግሎቶችን፣ ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ማስገባትም የእቅዱ አንድ አካል መሆኑ ተገልጿል።
እቅዱ ሰብዓዊ ድጋፍን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲሁም የግሉን ዘርፍ በተለይም የኢኮኖሚ እና ቢዝነስ እንቅስቃሴውን ዳግም ስራ የማስጀመር ዓላማም አለው።