በትግራይ እስካሁን ከ40 ሺ ለሚልቁ ሰዎች የኮሮና ክትባቶችን ለመስጠት ተችሏል ተባለ
የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ለማድረግ እንዲችሉ ለ15 የግል ህክምና ተቋማት ፈቃድ መሰጠቱም ነው የተገለጸው
በክልሉ ባለፉት 2 ወራት በቫይረሱ ምክንያት የ17 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል
በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በፊት በማይጨው፣ ውቅሮ፣ አዲግራት፣ አክሱም፣ ሽሬ፣ ሁመራ እና መቀሌ በድምሩ 6 የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማዕከላት ነበሩ።
ይሁንና ከእነዚህ ማዕከላት ውስጥ ከመቀሌው ውጪ ቀሪዎቹ በክልሉ በነበረው ጦርነት መውደማቸውን የክልሉ የኮሮና ቫይረስ አስተባባሪ ዶ/ር ሀርነት አዳነ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማዕከል ያለው በመቀሌ ብቻ ነው፡፡ ማዕከሉ በከተማዋ እና በዙሪያዋ ብቻ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እና የለይቶ ህክምና አገልግሎት በመስጠትም ላይ ይገኛል ከመጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ዳግም መጀመሩን እንደነገሩን እንደ ዶ/ር ሃርነት ገለጻ።
እስካሁን ከተመረመሩት 2 ሺህ 369 ሰዎች መካከል ቫይረሱ በ859 ላይ ተገኝቷል፡፡ 17 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።
በቫይረሱ ከተጠቁ 859 ሰዎች ውስጥ 38ቱ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡
110 ለሚሆኑ ከቫይረሱ ላላገገሙ ሰዎች የህክምና ክትትል እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሀርነት አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎች ዕጥረት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የቫይረሱ ስርጭት በመጨመር ላይ በመሆኑ የምርመራ አቅምን ለማሳደግ ለ15 የግል ህክምና ተቋማት ምርመራ ማካሄድ የሚያስችላቸው ፈቃድ እንደተሰጣቸውም አስተባባሪው ተናግረዋል።
በመቀሌ ብቻ ተወስኖ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እና ሌሎች ስራዎችን ለማከናወን ተፈናቃይ ዜጎች ባሉባቸው መጠለያዎች በማይጨው፣ በውቅሮ፣ በአዲግራት እና በአክሱም ተጨማሪ በበቂ ግብዓት የተደራጁ ማዕከላትን ለመክፈት ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው።
እንደ ዶ/ር ሃርነት ገለጻ ይህ መሆኑ በተወሰነ ደረጃ ችግሩን ሊያቀል ይችላል፡፡
ከፌደራል መንግስት የተገኙ 6 አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ስልጠና ላይ መሆናቸውን የገለጹት አስተባባሪው መንግስት ክልሉ ያለበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በትራንስፖርት፣ በበጀት እና ሌሎች አጋዥ የህክምና መሳሪያዎች ያጋጠሟቸውን እጥረቶች እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡
ክልሉ 119 ሺህ ዶዝ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የተመደበለት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ40 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ክትባቱ መሰጠቱንም ተናግረዋል።
ክትባቱን በመቀሌ እና መብራት ባለባቸው ማይጨው፣ አዲግራት፣ አድዋ፣ አክሱም እና ሽሬን መሰል ከተሞች ነው የተሰጠው፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የጤና መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን ተከትሎ ክትባቶቹን ወደ ገጠር ወረዳዎች እና ሌሎች አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ለመስጠት አልተቻልም ሲሉም አክለዋል አስተባባሪው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ወንድወሰን እሸቱ በበኩላቸው አጋዥ መተንፈሻ መሳሪያዎች እንደ አገር ያጋጠመ ችግር መሆኑን ተናግረው ተጨማሪ 530 አልጋዎች ከውጭ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ በመግባት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።