አሜሪካ ከትግራይ ግጭት ጋር በተያያዘ በባለስልጣናት ላይ የጉዞ እግድ ለመጣል ወሰነች
የኢትዮጵያ መንግስት ጣልቃገብነትን እንደማይቀበል ማስታወቁ ይታወሳል
አሜሪካ የምትጥለው የጉዞ እግድ በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ እንደሚሆን ብሊንከን በመግለጫው አስታውቀዋል
የአሜሪካ መንግስት ለትግራይ ክልል ግጭት ኃላፊነት አለባቸው ባላቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ እግድ ለመጣል መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው “ለግጭቱ ኃላፊነት መውስድ አለባቸው ብለን ባመናቸው አካላት ላይ ማእቀብ ለመጣል ዝግጅት ጀምረናል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ብሊንከን በትግራይ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም በተደጋጋሚ እንዲቆም ድምጻቸውን ማሰማታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ብሊንከን የጉዞ እግዱ በቀድሞ እንዲሁም አሁን ስልጣን ላይ ባሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ባለስልጣናትና በትግራይ ክልል ቀውስ የተሳተፉ የአማራ ክልል መደበኛ ያልሆኑ ሃይሎችና ግጭቱ መፍትሄ እንዳያገኝ ያደረጉ ወይም የተባበሩ የህወሓት አባላትን ያካትታል ብሏል፡፡
ሚኒስቴሩ አክሎም አለምአቀፍ ማህበረሰቡ እርምጃ የሚወስድበት “ወቅት አሁን ነው” ብሏል፡፡
እገዳው የሚጣለው ተገቢ ያልሆነ ግጭት ያስነሱና የትግራይ ህዝብን ያጠቁ እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ ባደረጉ ባለስልጣናት ላይ መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
እገዳው፣ እገዳ የተጣለባቸው ግለሰቦች ቤተሰቦችምን ያጠቃልል ብሏል መግለጫው፡፡ ከጉዞ እግዱ በተጨማሪ መጠነ ሰፊ የሆነ የኢኮኖሚና የጸጥታ ድጋፍ እግድ እንደሚኖር በመግጫው ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ያልተገቡ ክሶች እና ዘመቻዎች በኢትዮጵያ ላይ እየተደረጉ ነው ሲል ከሰሞኑ ዝርዝር መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
መንግስት በእንዲህ ዓይነት ኢ-ፍትሐዊ ዘመቻዎች ኢትዮጵያን ከልክ ባለፈ ጫና ውስጥ ለማስገባት የሚደረገው ጥረት ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ የሚያባብስ መሆኑን በመጠቆም ጫና ለማድረግ ከሚሞክሩ አጋሮቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በድጋሚ ለማጤን ሊገደድ እንደሚችልም አስታውቋል፡፡
በትግራይ ክልል ውስጥ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ክልሉን ሲመሩ የነበሩ የህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ጦር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር።
በክልሉ ግጭቱን ተከትሎ የንጹሃን ግድያና ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በግጭቱ ተሳታፊ ሃይሎች መፈጸማቸው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ና በተለያዩ የአለምአቀፍ የመብት ድርጅቶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መጥቀሱ ይታወሳል፡፡