ትግራይ ክልል የነበረችው “ሳውኔ” ቀበሌ በአፋር ክልል ስር መተዳደር ጀምራለች ተባለ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በወሰን ጉዳይ ላይ ሕግና ስርአትን ተከትሎ ምላሽ ይሰጣል ብሏል
የአፋር ክልል የአስተዳደር መዋቅር ዘርግቶ ቀበሌዋን እያስተዳደረ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ለአል ዐይን አረጋግጠዋል
በአፋር ክልል ዞን ሁለት ዳሎል ወረዳ እና በትግራይ ክልል ምሰራቃዊ ዞን በሳዕሲዕ ፃዕዳ እምባ ወረዳ መካከል የምትገኘው “ሳውኔ” ቀበሌ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስር መተዳደር መጀመሯ ተገለጸ፡፡
የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አሊ ዲኒ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ፣ “ሳውኔ” ቀበሌ በትግራይ ክልል ስር እንድትተዳደር የተደረገው “ከሕግ ውጭ በኃይል ስለነበር አሁን ተመልሳ በአፋር ስር እየተዳደረች ነው” ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል ስር የነበረችው ቀበሌዋ ከዓመታት በኋላ ”ሕዝብ ወደፈሚፈልገው ተመልሳለች” ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
የቀበሌው ነዋሪዎች በአፋር ክልል ስር እንዲተዳደሩ እንዲፈቀድላቸው ከሰባት ዓመታት በፊት ጥያቄ አንስተው እንደነበር ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአፋር ክልል ባለስልጣን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ከሰባት ዓመት በፊት ጥያቄውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበው እንደነበር የገለጹት የሥራ ኃላፊው በዚህም ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ከትግራይ ክልል የልማት ሴፍቲኔት ፣ የጤና እና መሰል አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ እንዳያገኙ አድርጓቸው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ለአብነትም በየጊዜው ይሰጥ የነበረውን የፖሊዮ ክትባት የቀበሌዋ ነዋሪዎች ሳያገኙ እንደቆዩ የሥራ ኃላፊው ይናገራሉ፡፡
“ሳውኔ” ቀበሌ አፋርኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎች የሚነገሩባት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ቀበሌዋ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በትግራይ ክልል ስር የነበረች ቢሆንም አሁን የአፋር ክልል መንግስት የአስተዳደር መዋቅር ዘርግቶ ማስተዳደር መጀመሩን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አሊ ዲኒ አረጋግጠዋል፡፡ አካባቢው ወደ አፋር ክልል የተጠቃለለው ጥቅምት 24 ቀን 2013 አ.ም ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ከተገለጸ በኋላ የአፋር ክልል ልዩ ሀይል ከመከላከያ ሰራዊት ጋራ በመሆን የአጸፋ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ የህገ-መንግስት አስተምህሮና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ከሰሞኑ ውይይት ባደረገበት ወቅት የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰን ጉዳይ ሕግና ስርአትን ተከትሎ ህዝብን መሰረት በማድረግ በአስቸኳይ ምላሽ በሚያገኝበት ጉዳይ ዙሪያ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር መክሯል።