ትምህርቱን በተያዘው የትምህርት ዓመት ለመጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉንም ክልሉ አስታውቋል
ትግራይ ክልል ግእዝን በመደበኛ ትምህርት መርሀግብር ሊያስተምር ነው
በትግራይ ክልል የግእዝ ቋንቋን በመደበኛ የትምህርት መርሀ ግብር ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ቋንቋዎች አካዳሚና ትምህርት ቢሮ አስታወቁ።
የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር ዳንኤል ተክሉ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት በሀገሪቱ በግእዝ ቋንቋ የታተሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጥንታዊ የብራናና የመጽሀፍት ህትመቶች አሉ።
“አዲሱ ትውልድ ፅሁፎችን በማንበብ የሀገሩን ባህልና ቋንቋ እንዲሁም ታሪክና ማንነት ጠንቅቆ እንዲያውቅ ለማበረታታት የቋንቋውን ትምህርት መስጠት አስፈልጓል” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
ትምህርቱን በተያዘው የትምህርት ዓመት በክልሉ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል ።
ከትግርኛ፣ ኩናምኛና ሳሆኛ ቋንቋዎች ቀጥሎ ግዕዝ 4ተኛ ቋንቋ ሆኖ በክልሉ በሚገኙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊነት ወስዶ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የመማር ማስተማር ስራው እንዲጀመር በክልሉ ምክር ቤት በአዋጅ መጽደቁንም አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትን በክልሉ በሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማስጀመር የመምህራንና የመማሪያ መፃፍት ዝግጅት እየተደረገ ነው።
ከስድስት ወራት በኋላ ትምሀርቱን ለመጀመር እቅድ መያዙን አመላክተዋል ።